በአማራ ክልል በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ጥሬ ገንዘብና ንብረት መባከኑን ተጋለጠ፡፡

በአማራ ክልል በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ጥሬ ገንዘብና ንብረት መባከኑን ተጋለጠ፡፡
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ/ም) የምክር ቤቱን አባላት ያነጋገረና ከፍተኛ ጥያቄ ያስነሣ የ2010 ዓ.ም የክዋኔ ኦዲት የስድስት የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የኦዲት ግኝት ይፋ ተደርጓል፡፡
ዋና ኦዲተሩ ረዳት ፕሮፌሠር ገረመው ወርቁ ለምክር ቤቱ ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ጥሬ ገንዘብና ንብረት መባከኑን ተናግረዋል፡፡
ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት የጐንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ፣ የእንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ፣ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ የሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም /ዩራፕ/፣ የጤና ጥበቃ ቢሮ እና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በዓመቱ ውስጥ ኦዲት አድርጐ ያጠናቀቃቸውና ከፍተኛ ጉድለት የተገኘባቸው መስሪያ ቤቶች መሆናቸውን አጋልጧል፡፡
ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው ተቋማቱ ሥራዎችን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ አልፈጸሙም፡፡
ከአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ የህክምና መሣሪያዎችን ከአስር ዓመት በላይ ካለ አገልግሎት እንዲቀመጡ ያደረጉት የጐንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ማባከናቸው በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል፡፡
በሪፖርቱ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ለኢትዮጵያ መድሀኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ከከፈለው የቅድመ ክፍያ ሂሣብ መካከል ከ235 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያላቸው ዕቃዎች ከአምስት ዓመታት በላይ ተገዝተው አለመቅረባቸውም ተመላክቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ በሁሉም ዞኖች ከ2005 እስከ 2009 ዓ.ም ብቻ ከሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስወጡ የእንስሳት መድሀኒቶች ጥቅም ላይ ሳይውሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ማለፉ ተመልክቷል፡፡
ሪፖርቱ በክልሉ በብድር መልክ ለዩራፕ መንገድ ግንባታ ለተቋራጮችና አማካሪዎች ያለ አግባብ ከ15 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በመክፈል እንዲመዘበር መደረጉ ተጋልጧል፡፡
በህይወት በሌሉ፣ በማይታወቁና ተገቢነት በሌላቸው ግለሠቦች ስም የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትናመስሪያ ቤት ከፍተኛ ሀብት መመዝበሩንም በጉባኤው ተጋልጧል፡፡