የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢህአዴግ መንግስት አመራር እስካለ ድረስ ለችግራቸው መፍትሄ እንደማያገኙም ተናግረዋል።
የገዢው መንግስት ‹‹… ድርቁ ሊያስከትል የነበረውን አደጋ ተቆጣጥረናል፤ በየአከባቢው ተገቢውን እርዳታ ለተጎጂዎች እያደረስን ነው….››ቢልም ፤ በምስራቅ አማራ የትግራይ ድንበር አካበቢ የሚገኙ ተጎጅዎች ሰሞኑን እንደተናገሩት ፡- በአንድ ቀበሌ ብቻ በደረሰው ድርቅ በከፍተኛ ደረጃ የተጎዱ አምስት ሽህ ያህል ሰዎች እርዳታ ሳይደርሳቸው በችግር ላይ ይገኛሉ፡፡ በረሃቡ ምክንያት ከሰው ህይወት መጥፋት ጀምሮ ንብረታቸው ሲያልቅ በድንጋጤ ታንቀው እስከ መሞት የደረሱ ሰዎች እንደነበሩ የአቋሽሜ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ሙሉ አባተ ገልጸዋል፡፡
በአቋሽሜ ቀበሌ በሚገኙ አስር ጎጦች ውስጥ ከሚገኙ ተጎጂዎች መካከል በእያንዳንዳንዱ ቤት ሁለትና ከዚያ በላይ ወገኖቻችን በመሰደድ ቀያቸውን ጥለው እንደሄዱ የተናገሩት የቀበሌው ሊቀመንበር፣ በተለይ የወጣቱን ብዛት ለመቁጠር እንደሚያዳግት ያስረዳሉ።
በቀበሌዋ ከሚገኙ አስር ጎጦች በአንድ ጎጥ ላይ ብቻ 50 አባወራዎች ጥለው በመሄዳቸውና በሌሎችም አካባቢዎች እስከ 15 አባወራዎች አካባቢውን ጥለው በመሰደዳቸው፣ በቀበሌው በተደረገው ቆጠራ ባጠቃላይ ከ200 በላይ አባዎራዎች ቤታቸውን ዘግተው ለልመና እንደተሰማሩ ሊቀመንበሩ ይገልጻሉ፡፡
‹‹በቀበሌያችን ከሃምሌ ወር ጀምሮ የሚቀመስ ምግብ የለም፡፡››የሚሉት ሊቀመንበሩ ‹‹እንስሳት በተለይ ከብቶችና ፍየሎች ያለቁት ዝናብ ለረጅም ጊዜ ባለመዝነቡ ምክንያት ምንም ቀለብ ባለመኖሩ ነው፡፡›› ይላሉ፡፡ በስደት ቀያቸውን ለቀው የሄዱት አባወራዎችና ወጣቶች በሄዱበት አካባቢ የሚሰሩት በማጣታቸው እና የገዢው መንግስት እገዛ ባለመኖሩ በመቸገራቸው ተመልሰው ለመምጣት ቢፈልጉም፣ መመለስ ያልቻሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ያክላሉ፡፡
‹‹መንግስት አልደረሰልንም ! ›› የሚሉት ሊቀመንበሩ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም ስንዴ ውሰዱ ቢባሉም እህሉን እንዲረከቡ የተደረገበት የእርዳታ ጣቢያ በመራቁ ተረጂዎች እህሉን ተቀብለው በመሸጥ ለትራንስፖርት ከማድረግ ውጭ ወደ ቀያቸው አምጥተው ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ሁኔታ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ለተጎጂዎች ተብሎ በሚቀርበው ቀለብ ተጠቃሚ መሆን የቻለ አንድም የቀበሌቸው ተጎጅ እንደሌለ ሊቀ መንበሩ አክለዋል።
‹‹ በቀጣይ እርዳታው በተገቢው መንገድ ካልቀረበ የሰው ህይወት ማለፉ ይቀጥላል፡፡›› የሚሉት የቀበሌው ሊቀመንበር፣ የህውሃት/ኢህአዴግ አመራር ባሉበት ሁሉ ችግሩ ምንጊዜም መፍትሄ ይገኛል የሚል ሃሳብ እንደሌላቸው በተለይ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡
ከብት ያላቸውን ‹‹እርዳታው አይመለከታችሁም!››በማለት ከብቶቻቸውን ሸጠው እንዲጠቀሙ ቢወሰንባቸውም ከብቶቻቸውን ሸጠው ለመጠቀም የሚያስችል የገበያ ትስስር ባለመመቻቸቱ ባለሃብቶችም የሚቀምሱት በማጣት ባዶ እጃቸውን ወደ ስደት ለመሄድ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ በስደት ሄደው ችግር ውስጥ ያሉ ተጎጂዎችን ለመመለስ ገንዘብ በማዋጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን የተናገሩት የቀበሌው ሊቀ መንበር፣ በቀያቸው እስካሁን የደረሰ እርዳታ ባለመኖሩ የገዢው መንግስት እርዳታውን ቀበሌያቸው ድረስ እንዲያደርስላቸውና በውሃ እጥረት ምክንያት እየደረሰባቸው ያለውን ችግር ለማስወገድ ወደ ቀበሌያቸው የሚደርስበትን መንገድ አመራሩ ያመቻችላቸው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡
የገዥው መንግስት በየአካባቢው በተፈጠሩበት የውስጥ ችግሮች ምክንያት በድርቅ የተጎዱትን ወገኖች ችላ በማለት ተገቢውን የቤት ስራ ባለመስራቱ ተጎጂው ህብረተሰብ አሁንም በየከተሞች መንገድ ላይ በመዘዋወር በመለመን ላይ ናቸው፡፡