ሚያዝያ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በሲሚንቶ እጥረት ግንባታዎች እንዲቋረጡ መደረጉን በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎችና በግንባታ ላይ የሚገኙ የህብረተሰቡ ክፍሎች ለዘጋቢያችን አስታውቀዋል፡፡
ችግሩ የህወሃቱ ንብረት በሆነው መሰቦ ስሚንቶና የሼክ አላሙዲን ንብረት በሆነው ደርባን ስሚንቶ መካከል ባለው ውዝግብ የተፈጠረ ነው ይላሉ ነጋዴዎች። በዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ ለአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ80 እስከ 100 ብር ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍል
እየተደረገ ነው።
በባህርዳር ከተማ በሲሚንቶ ንግድ ስራ ተሰማርቶ ለረዢም ጊዜ የሰራው ወጣት ሱሌይማን አሊ ፤ በአማራ ክልልና በመላው ኢትዮጵያ ለረዢም ጊዜ ተጽኖ ፈጥሮ የነበረውን የመሶቦ ሲሚንቶ ዋጋ የደርባን ሲሚንቶ ፋብሪካ ምርት እንዲቀንስ አድርጎት ነበር ይላል።
ገዢው ፓርቲ ጥንታዊው የሙገር ሲሚንቶ ምርት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እንዳይገባ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የውስጥ ትዕዛዝ መከልከሉ ያወሳው ነጋዴ ሱሌይማን ፣ በዚህ እገዳ ምክንያት በጥራቱ የታወቀውን የሙገር ምርት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ
በሚያጓጉዙ መኪኖች ላይ ኮንትሮባንድ እቃ እንደጫኑ ተቆጥሮ እንዲቀጡ የሚደረግ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ ህብረተሰቡ ሳይወድ በግድ የመሶቦ ምርቶችን እንዲገዛ ተገዶ ቆይቷል ብሎአል።
ከሁለት ወር በፊት ለመሶቦም ሆነ ደርባን ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ገንዘብ ገቢ አድርገው ምርቶቹ እንዲላኩላቸው ቢጠባበቁም መልስ ማጣታቸውን ነጋዴዎች ይናገራሉ።