ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-የክልሉን መምህራን ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ መንግስቱ አህመዴን ከስልጣን ለማውረድ በተጀመረው እንቅስቃሴ መምህራን እልህ ውስጥ መግባታቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ መምህራን ተነግረዋል።
ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት የመምህራን ማህበር መምህራንን በተደጋጋሚ ስብሰባ በመጥራት አዳዲስ አመራሮችን እንደሚርጡ ለማግባባት ሙከራ ቢያደርግም፣ መምህራን ግን አሁንም በማህበራቸው መሪ ጽኑ እምነት እንዳላቸው በመጥቀስ የመንግስትን ማግባባትና ጫና አልተቀበሉትም።
በሰሜን ጎንደር፣ በምእራብ ጎጃምና በሰሜን ሸዋ የሚገኙ አንዳንድ መምህራን መንግስት በያዘው ጫና ባለመደሰት ራሳቸውን ከማህበሩ አግልለዋል።
አንዳንድ የማህበሩ አባላት ለማህበሩ ስራ ማስኪያጃ እየተባለ በየወሩ የሚቆረጠው ገንዘብ፣ ከእንግዲህ ያለፍላጎታችን እንዲቆረጥብን አንፈልግም የሚል ደብዳቤ ማስገባታቸውን ገልጠዋል።
የአማራ ክልል መምህራን ማህበር እና መንግስት ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
መምህር መንግስቱ በአገር አቀፉ የመምህራን ማህበር ጉበኤ ላይ የመምህራንን የደሞዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገትና የማስተማርና ሀሳብን የመግለጽ፣ ከሁሉም በላይ መምህራን ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ እንዲሆኑ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር መብታቸውን እንዲጠይቁ ሊፈቀድላቸው ይገባል የሚል ሀሳብ መሰንዘራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።