በአማራ ክልል ሊካሄዱ የታሰቡ የኢንዱስትሪ ልማቶችን ለመደገፍ የተመደበ 4.5 ቢሊዮን ብር ለትግራይ ክልል መተላለፉ በብዓዴን አባላት ዘንድ ቁጣ ቀሰቀሰ

ኢሳት (መስከረም 11 ፥ 2009)

በቅርቡ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአማራ ክልል ሊካሄዱ የታሰቡ የኢንዱስትሪ ልማቶችን ለመደገፍ ሲሰጥ የነበረ 4.5 ቢሊዮን ብር ለትግራይ ክልል መተላለፉ በብሄረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብዓዴን) አባላትና ደጋፊ ዘንድ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተገለጸ።

የፓርቲው አመራሮች ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ ባካሄዱት ልዩ ጉባዔ ወቅት የዚህ ገንዘብ ዝውውር ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡንና በድርጊቱ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ጠንካራ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተሳታፊ እማኞች ለኢሳት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለክልሎች በሚሰጠው ልዩ ድጋፍ በአማራ ክልል ለሚካሄዱ የማምረቻና የኢንዱስትሪ ልማት ድጋፎች 4.5 ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ እንደነበር ታውቋል።

ይሁንና በጀቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቀርበውበት ወደ ትግራይ ክልል እንዲዛወር መደረጉንና ጉዳዩ በፓርቲው ልዩ ስብሰባ ወቅት መከራከሪያ ሆኖ መነሳቱን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የክልሉ ባለስልጣናት ለተነሳው ጥያቄ ምላሽን ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም የብዓዴን አመራር የሆኑት አቶ በረከት ሰምዖን የአማራ ክልል በቂ የፕሮጄክት ቀረጻ ባለማከናወኑ ምክንያት ገንዘቡ ለክልሉ ሳይሰጥ መቅረቱን ምላሽ እንደሰጡ በጉባዔው የተገኙ ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።

ይሁንና በርካታ ተሳታፊዎች የብዓዴን አመራሮች ለክልሉ የሚያስቡ ከሆነ ፕሮጄክቱ ስኬታማ እንዲሆነ ለምን ሙያዊ ድጋፍ እንዳልሰጡ ጠንካራ ጥያቄን ማቅረባቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

አቶ በረከት ስምዖን በጀቱ የተሻለ ለሰራ ክልል ተላልፏል ሲሉ የሰጡትን ምላሽ ተከትሎ ተሳታፊዎች ቁጣ ማሰማታቸውን የተናገሩት እማኞች ጉባዔው በልዩነት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

ከሃምሌ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ህወሃት በበላይነት እየተቆጣጠራቸው ያሉ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በዚሁ ጉባዔ መከራከሪያ ሆነው እንደቀረቡም እማኞች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

የጄኔራል ሹመቶችን ከአንድ ብሄር ብቻ ስለመሆኑ ተጠይቀው የነበሩት አቶ በረከት ስምዖን ሹመቱ የረጅም አመት የስራ ልምድን ግምት ውስጥ አስገብቶ የተከናወነ እንደሆነ ምላሽ መስጠታቸውም ታውቋል።