በአማራ ክልል ህዝቡ በደን ኢንተርፕራይዝ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱን ተከትሎ ድርጅቱ ሊዘጋ ነው

የካቲት ፯ ( ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአማራ ደን ኢንተራፕራይዝ በህዝብ ተቀባይነት ማግኘት ባለመቻሉ እና በኪሳራ ውስጥ በመግባቱ የክልሉ መንግስት በክልሉ 14 ቦታዎች ካቋቋመ በኋላ ሊዘጋው እንደሆነ ታውቋል፡፡
በርካታ አነስተኛ የጣውላ ማሽኖችን ከአንዶነዥያ በማስመጣት ወጣቶችን የስራ ዕድል በመንጠቅ እና ግዙፍ ደኖችን በማውደም በርካታ ጣውላዎች ማምረት ቢችልም ፣ ላለፉት አምስት አመታት ያመረታቸው ጣውላዎች አገልግሎት ላይ መዋል ባለመቻላቸው ለብልሽት ተደርገዋል፡፡ ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ያመጣል ተብሎ ቢታሰብም አንድም ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችለውን እድል ባለማግኘቱ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ መግባቱ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ስዓት ከማህበረሰቡ ጋር በተካሄዱ ውይይቶች ማህበረሰቡ ኢንተርፕራይዙን በጥሩ አይን እያየው ባለመሆኑ ተቋሙ ሊታጠፍ ካልያም ለስራ አጥ ወጣቶች በበድር ሊተላለፍ ይችላል ተብሏል፡፡
ሰሞኑን አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ከምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም እና ከአዊ ዞን ከተመረጡ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ከህብረተሰቡ ጋር በቂ ውይይት ሳያደርግ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተተከሉ ደኖችን መቁረጡ አግባብ አለመሆኑን እና ምንም አይነት ማህበረሰባዊ ጠቀሜታ የሌለው ተቋም መሆኑን ተወካዮቹ ገልጸዋል::
ልጆቻችን ለአፈር መሸርሸር ከሚዳርጉ መንስኤዎች ውስጥ ጥቀሱ ሲባሉ “ ልቅ ግጦሽ፣ የደን መመንጠር እና የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ” ይላሉ ያሉት ኗሪዎች፣ የደን ኢንተርፕራይዙ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተተከሉ ደኖችን መመንጠሩ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን እያስቆጣ ነው ሲሉ ከምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም እና ከአዊ ዞን የተወከሉት አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
ተወካዮቹ “በአንድ በኩል አረንጓዴ ልማት ይባላል በሌላ በኩል ግን ደን ይጨፈጨፋል” በማለት ገልጸው፣ ለአብነትም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ መግቢያ ላይ የሚገኘው ሰው ሰራሽ ደን በአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ መቆረጡ እንዳበሳጫቸው ይናገራሉ። አቶ ቢተው አይናለም እንደሚሉት በ1975 ዓ.ም አካባቢ እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ተራራማው መሬት በጐርፍ እንዳይታጠብ በማሰብ የተተከለውና ከፍተኛ ጥበቃ ተደርጐለት ያደገው ደን ብዙም ውይይት ሳይደረግበት መቆረጡ እሳቸውንም ሆነ ሌሎችን የአካባቢውን ኗሪዎች አስከፍቷል:: “ደኑ ለጥቅም ሲደርስ መቆረጥ እንዳለበት እንስማማለን” የሚሉት አቶ ቢተው፣ ደኑ ከተቆረጠ በኋላ በአግባቡ አለመተካቱና ለለፋው ህብረተሰብ አንዳች ነገር አለመደረጉ አሳዝኖናል ሲሉ ያክላሉ፡:
አቶ ቢተው የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ቆረጣውን ከማካሄዱ በፊት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ሳይመካከር በአመቺው ጊዜ ቆረጣውን ስለማያካሂድ ደኑ መልሶ ማቆጥቆጥ ሳይችል መቅረቱን ይጠቅሳሉ:: ለዚህ ማሳያቸው ደግሞ በባንጃ ወረዳ ከእንጅባራ ከተማ ወደ ቻግኒ በሚወስደው መንገድ ላይ ያለ ያለወራቱ የተቆረጠው እና ሳያቀጠቅጥ የቀረው የባህር ዛፍ ደን ነው:: አቶ ቢተው፣ የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ቀደም ሲል የለሙ ደኖችን ለመጠቀም የሚያደርገው ቆረጣ በተገቢው መንገድ የማይመራ ከሆነ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ:: ምክንያታቸው ደግሞ ኢንተርፕራይዙ ደን ከመመንጠር ውጭ አንዳች ነገር ተክሎ አላሳየንም የሚል ነው::
ሌላው የእንጅባራ ከተማ ዙሪያ ነዋሪ አቶ ካሳሁን ቢተውም የአማራ ደን ኢንተርፕራይዙ የሚያካሂደው የደን ቆረጣ ጊዜውን ያላገናዘበና ከህብረተሰቡ ጋርም ምክክር ያልተደረገበት ነው ሲሉ ይገልጻሉ:: “በቦታው የሚገኙት በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተተከሉ ደኖች ዝም ብለው የተገኙ ሳይሆኑ ህዝቡ ፀሐይ፣ ዝናብና ብርድ እየተፈራረቀበት ተክሎ ያሳደጋቸው ናቸው፤ እነዚህን ደኖች ለጥቅም ማዋል ሲፈለግ ህብረተሰቡ እንደ ባለቤት ምን እናድርግ በምን መንገድ ጥቅም ላይ እናውላቸው? በምን ወር እንቁረጣቸው? እንዴት እንተካቸው?” በሚሉት ላይ መወያየት ነበረበት ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ::
ኢንተርፕራይዙ ግን እኛን ሳያማክር ግማሹን በጨረታ ሌላውን ደግሞ በራሱ መንገድ እየቆረጠ አካባቢውን ደን አልባ እና ምድረ በዳ እያደረገ ነው ፣ በዚህ ምክንያት ማህበረሰቡ ለኢንተርፕራይዙ ያለው አመለካከት መልካም አይደለምም ሲሉ ያክላሉ።
“ኢንተርፕራይዙ ዛፎችን ከመቁረጡ በፊት ችግኝ አፍልቶና ተክሎ ማሳየት ይገባው ነበር” የሚሉት አቶ ካሳሁን፣ “ ይህን ሳያደርግ ደን መመንጠር ግን መንግስት በተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ዙሪያ ከሚሰራውና ለማግኘት ካሰበው ውጤት ጋር አብሮ የሚሄድ አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረዋል:::
ኢንተርፕራይዙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ባለመስራቱ ለአብነት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ብቻ ደገራ አቦና አርሳገንባሃ የመሳሰሉ ሰው ሰራሽ ደኖች ተቆርጠው ሳያገግሙ ቀርተዋል:: ይህን ተከትሎ የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ አመራሮችን ያነጋገሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርም ይሁን በሌሎች በምስራቅ ጐጃምና በደቡብ ጐንደር አካባቢ ያሉ ደኖች መጨፍጨፋቸውን ተከትሉ ህዝቡ ሊቀበለው ባለመቻሉ ተቋሙም ትርፍማ መሆን ባለመቻሉ በአማካሪዎቻቸው ጥናት ተደርጎ ሊፈርስ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡
ባለፉት አመታት በክልሉ በሚገኙ 46 የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ደን ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ በአጠቃላይ ከአስራ ዘጠኝ ሺህ 200 ሄክታር በላይ ደን በኢንተርፕራይዙ ተመንጥሯል::