ጥቅምት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ህወሃት/ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ኮማንድ ፖስት በሚል ባቋቋመው የአፈና መዋቅሩ የአማራ ክልል ወጣቶችንና የመንግስት ሰራተኞችን ኢላማ በማድረግ ከፍተኘ ስቃይ እየፈጸመ ነው። ህወሃት የበቀል ጅራፉን በክልሉ ዜጎች ላይ አሳርፎአል የሚሉት ነዋሪዎች፣ ድርጊቱ ወደ አልተፈለገ ደም መፋሰስ ሊያመራ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው።
ባለፉት አራት ቀናት በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በርካታ ወጣቶች ታፍሰው በገፍ ወደ እስር ቤት እየተወሰዱ እየተደበደቡ ነው። ባህርዳርና ጎንደር ልዩ የህወሃት አገዛዝ የአፈናና ድብደባ ኢላማ የሆኑ ቢሆንም፣ አፈናው ወደ መለሰተኛ ከተሞች ተሸጋግሮአል። በጢስ አባይ አፈናውን የተቃወሙ ማንነታቸው ያልታወቁ ሃይሎች 4 የአጋዚ ወታደሮችን ገድለዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ የመሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ሰለሞን አራጌ ተይዘው ወደ እስር ቤት ሲወሰዱ መምህራን መምህሩ ታስሮ ወደ ሚገኝበት እስር ቤት በማምራት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል። ይህን ተከትሎ ተማሪዎች ትምህርት በማቆም አገዛዙን የሚያወግዙ መፈክሮችን እያሰሙ መምህራቸውም እንዲፈታላቸው የጠየቁ ሲሆን፣ ፖሊሶች ወደ አካባቢ ደርሰው ሰልፉን በትነውታል። ሰልፉን ተከትሎ ከ6 በላይ ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል።
መምህራኑ የስራ ባልደረባቸው እንዲፈታ ሲጠይቁ፣ ፖሊስ ጽ/ቤት “ እኛ አላሰርነውም፣ ያሰረው ኮማንድ ፖስቱ ነው፤ እኛ የምናውቀው ነገር የለም” በማለት መልሰውላቸዋል። በዚሁ ከተማ የመዘጋጃው የመዝገብ ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን፣ የሞጣ የንግድ ባንክ ካምቦ ቅርንጫፍ ም/ል ስራ አስኪያጅ፣ አቶ አንዱአለም ጸበሉ የተባሉ ሰዎች መታሰራቸው ታውቋል።
ከአዲሱ አመት መግቢያ ጀምሮ ተደጋጋሚ የተኩስ ድምጽ የሚሰማባት ሞጣ ከተማ ትናንትም በተኩስ ስትናጥ አምሽታለች። ዛሬ ለማወቅ እንደተቻለው የወብ ቀንጫሪ ሊቀመንበር ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በጥይት ተመትቶ ሆስፒታል ገብቷል። ሌላ የቀበሌ አማራርም እንዲሁ ትናንት የተደበደበ ሲሆን፣ ደብዳቢው ግለሰብ መታሰሩ ታውቋል። ሞጣ በከፍተኛ አፈና ውስጥ መሆኗን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በተለይ የመስቀል እለት ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ እና ሲተኩሱ የነበሩ ወጣቶችን ለመያዝ የሚደረገው እንቅስቀሴ ውጥረቱን እንዳባባሰው ተናግረዋል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ደባይ ጥላት ግን ወረዳ ባለፈው ቅዳሜ ከ10 በላይ ባለሃብቶች፣ መምህራንና የተለያዩ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ታስረዋል።
ነሃሴ 23 እና 24 ፣ 2008 ዓም ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ስታስተናግድ በነበረችው በሜጫ ወረዳ መራዊ ከተማ ደግሞ በቁጥጥር ስር የዋሉ በርካታ ወጣቶች ባህርዳር ወህኒ ቤት መታሰራቸውን ወኪላችን ከላከችው ዘገባ ለመረዳት ተችሎአል። ወህኒ ቤቱ ጥቅምት 18፣ 2009 ዓም በለጠፈው ማስታወቂያ ከሰኞ ጥቅምት 21 ቀን 2009 እስከ አርብ ጥቅምት 25 ቀን 2009 ዓም እስረኞችንና ቤተሰቦችን የማገናኘቱን ስራ በስብሰባ ምክንያት የማያስተናግድ መሆኑን በመግለጹ እና እገዳው ዛሬ የተነሳ በመሆኑ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እስረኞችን ለመጠየቅ በቦታው ተገኝቷል።
ፖሊሶች ዘመዶቻቸውን ሊጠይቁ ለመጡት ዘመዶች፣ “ እያንዳንዱ ጠያቂ ዘመድ ለታራሚዎች ያልሆነ መረጃ ከመስጠት ብትቆጠቡ ይሻላል፣ ይህን የተዛባ መረጃ ለታራሚዎች የምታወሩ ጠያቂዎች ከአገኘናችሁ ወንዱን በወንድ ፖሊስ፣ ሴቷን በሴት ፖሊስ በዱላ አስቀጥቅጠን ነገ ለፍርድ ቤት አቅርበን እናስቀጣችሁዋለን “ በማለት ሲናገሩ መዋላቸውን የገለጸቸው ወኪላችን፣ “የከተማው ና የገጠሩ ህዝብ በሙሉ በእስር ቤት ውስጥ እየኖረ መሆኑን ነው ለማረጋገጥ የቻልኩት” ስትል ትዝብቷን ገልጻለች።
በሰሜን ጎንደር ዞና በአለፋ ጣቁሳ ደግሞ ከ60 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ላለፉት 3 ሳምንታት ሲታሰሩ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት እንኳን አልቀረቡም። በከተማው ያለው ኮማንድ ፖስት ወጣቶችን በጅምላ እያሰረና እየደበደቡ መሆኑ፣ በርካቶች ቤታቸውን ጫካ ለማድረግ መገደዳቸውን ተናግረዋል። በዳርቅ ከተማም እንዲሁ ባለፉት 3 ቀናት ከ10 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ከስፍራው የደረን መረጃ ያመለክታል።
የእስርና የአፈናው እርምጃ በአማራ ክልል ብቻ የቆመ አይደለም። በኦሮምያና በደቡብም በተመሳሳይ መንገድ ቀጥሎአል። በተለይ በደቡብ ክልል የኮንሶን ህዝብ ጥያቄ ይደግፋል፣ ያስተባብራል የተባለ ዶ/ር ሃብቴ የተባለ ሃኪምና እና እናቱ በመኪና አደጋ መሞታቸውን የአካባቢው ወኪላችን ገልጿል። ዶ/ር ሃብቴ አገዛዙ በአካባቢው ህዝብ ላይ የሚፈጽመው ግፍ ሲቃወም የነበረ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ከግድያው ጀርባ የመንግስት እጅ አለበት ብለው ያስባሉ። ከሶስት ቀናት በፊት አስከሬኑ እንዲመረመር ወደ አዋሳ ቢላክም ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ምርመራው ተጠናቆ ወደ ቤተሰቡ አለመላኩ ታውቋል፡፡
ከወራት በፊት አርበኞች ግንቦት 7 በ ነጭ ሳር ፓርክ ጥቃት አካባቢ ጥቃት ካደረሰ በሁዋላ፣ በዚህ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ደብቃችሁዋል የተባሉ ሁለት በአሳ ማስገር የሚተዳደሩ ሰዎች በወታደሮች ትናንት የተገደሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ከአካባቢው እንዲበተኑ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አደባባይ በመውጣት የሚደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ በአፈናው ምክንያት ጋብ ያለ ቢመስልም፣ ዜጎች ራሳቸውን በማደረጃት ወደ ሃይል እርምጃ እየገቡ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ዞን ወጣቶች ራሳቸውን እያደራጁ የተለያዩ ጥቃቶችን እየፈጸሙ ነው። ባለፈው ቅደሜ በጢስ አባይ ከተማ በፒክ አፕ መኪና እየተዘዋወሩ ወጣቱን ሲያስጨንቁ የነበሩ የአጋዚ ወታደሮች መንደር በምትባለዋ ቀበሌ ላይ ሲደርሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የመኪናውን ጎማ በጥይት መትተው እንድትገለበጥ በማድረግ ፣ በላዩዋ ላይ የተሳፈሩት 4 የአጋዚ ወታደሮች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ ሹፌሩ ቆስሎ በህክምና ላይ ነው።
ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓም ከፌደራል ፖሊሶች ጋር ተዋግተው ከተገደሉት የአካባቢው የጎበዝ አለቃ አቶ ምክሩ ብርሃኑ በተደረገ የተኩስ ለውውጥ ሁለት ተጨማሪ የፌደራል ፖሊስ አባላት ተገድለው ተገኝተዋል።