የካቲት ፭(አምስት) ቀን፳፻፯ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራና በትግራይ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የትግራይ ክልል ህገወጥ በሆነ መልኩ ባደራጃቸው ታጣቂ ሚሊሺያዎች አማካኝነት ፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በጉልበት እየቀማ ነው በሚል ያስነሱትን ተቃውሞ ለመፍታት ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጡ ባለስልጣኖችና ከ300 ያላነሱ የህዝብ ተወካዮች ከሳምንታት በፊት ተሰብስበው መግባባት ባለመድረሳቸው ለየካቲት 4 በድጋሜ ቀጠሮ ከተያዘ በሁዋላ ፣ ትናንት ሊካሄድ የነበረው ስብሰባ በአንድ ቀን እንዲራዘም ከተደረገ በሁዋላ ፣ የካቲት 5 መጀመሩ ታውቋል።
ከክልሉና ከፌደራል ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጋር በመሆን ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጡ 15 የአካባቢው ነዋሪዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል ። ኢሳት ስብሰባው መጀመሩን ለማወቅ ቢችልም ፣ የስብሰባውን ሂደትና ውጤት ለማወቅ ሙከራ ቢያደርግም በአካባቢው ስልክ ኔት ወርክ እንዲጠፋ በመደረጉ ሳይሳካለት ቀርቷል።
በአካባቢው ከፍተኛ ሰራዊት መስፈሩን የሚናገሩት ምንጮች ፣ የትግራይ ክልል የመስፋፋት ፖሊሲውን ካልቀየረ ግጭት አይቀርም ይላሉ ። የትግራይ ክልል እስከመተማ ያለው ቦታ የትግራይ ክልል መሆኑን እየተናገሩ ሲሆን ፣ በአማራ ክልል የሚኖሩ ነዋሪዎች ደግሞ ቀድሞውንም ሁመራና አካባቢው በጉልበት መሰጠቱን በማስታወስ ፣ አሁን ክልሉ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጥብቀው ይቃወማሉ።
በአካባቢው የሚታየው ውጥረት አሁንም እንዳልበረደ የሚናገሩት ምንጮች ፣ በአማራ ክልል በኩል የሚኖሩ ነዋሪዎች የያዙት ጠንካራ አቋም የአማራ ክልል ባለስልጣናትን አጣብቂኝ ውስጥ ጥሎአቸዋል ።