ኢሳት (ጥር 15 ፥ 2009)
የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አልሸባብ ስልጠና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉ ሰባት ግለሰቦችን እስከ አራት አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሰኞ ወሰነ።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ በ2009 አም የጅሃድ ጦርነት በኢትዮጵያ ለማወጅ በማቀድ ወደ ደቡብ አፍሪካ በመሄድ በዚያ ከሚገኝ የአክራሪ የሽብር ቡድን ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ለሽብር ተግባር አባላትን በመመልመል ድርጊት ላይ መሳተፋቸውን በክሱ አመልክቷል።
ተከሳሾቹ በደቡብ አፍሪካ ስልጠናን ከወሰዱ በኋላ በ2006 አም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በተለያዩ ጊዜያት የሽብር ቡድን አባላትን በመመልመል በጅማ ከተማ በሚገኙ ጫካዎች ስልጠና መስጠታቸውም በክስ ቻርጁ መጠቀሱን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይሁንና በተከሳሾቹ ሰልጥነዋል ስለተባሉት ሰዎች የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ ሰባቱ ተከሳሾች ተጨማሪ ስልጠና በአልሸባብ ለመውሰድ ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በማዘጋጀት ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ተመልክቷል።
ተከሳሾቹ በቀረበባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ስለመሳተፋቸው በማስረጃ በመረጋገጡ እስከ አራት አመት ከአምስት ወር በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰኞ መወሰኑ ታውቋል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ለማስተባበል ሲከራከሩ ቢቆዩም አቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰነድና የሰው ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ውሳኔው ሊተላለፍ አመቻሉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
ጃፋር መሃመድ፣ መሃመድ ኑር፣ ሃጂ መሃመድ ታሚ፣ ሙዲን ጀማል፣ አህመድ አባ ቢያ፣ አንዋር ቲዳኔ፣ እና ሼህ ጀማል አባ ጨቦ በስም የተጠቀሱ ሰባቱ ተከሳሾች መሆናቸን ለመረዳት ተችሏል።
አምስቱ ተከሳሾች በአራት አመት እንዲሁም ሁለቱ ተከሳሾች ደግሞ በአራት አመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በደቡብ አፍሪካ ይገኛል ስላለው አክራሪ ቡድን የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።