በአላማጣ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ቀኑን ሙሉ በልዩ ሀይሎች ታግተው ዋሉ

ጥር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ጋርቬ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ጧት ወደ ስራ ለመሄድ ሲነሱ አካባቢያቸው በሙሉ በፌደራል    ልዩ ሀይል ፖሊሶች ተከቦ አግኝተውታል። ማንም ከቤት እንዳይወጣ በማገድ የመንግስት ባለስልጣናት በስም ጽፈው የያዙዋቸውን ከ300 በላይ ቤቶች ሲያስፈርሱ ውለዋል።

በእያንዳንዱ ቤት በር ላይ ሁለት ሁለት ልዩ ፖሊሶች ቆመው የእያንዳንዱን ሰው ቤት እንቅስቃሴ በሚከታተሉበት ሁኔታ የተለያዩ ሰዎችን አግኝቶ ለማነጋገር ባይቻልም አንድ ከቤት እንዳይወጡ የታገዱ ሰው እንደገለጡት ለመጸዳዳት እና ልጆቻቸውን ለማጫወት እንኳን ከቤት ሳይወጡ ታግደው መዋላቸውን ገልጸዋል።

ቤት አፍራሽ ግብረሀይሎች ቀኑን ሙሉ ሲያፈርሱ ውለው አካበቢውን ከ11 ሰአት በሁዋላ ለቀው የሄዱ ሲሆን ፣ ንብረቶቻቸው ሜዳ ላይ የወደቁባቸው ሰዎች ራሳቸውን ስተው ሲወድቁ ዘግይቶ ያነጋገርነው አንድ የአይን እማኝ ገልጿል 

ባለፈው ጥር ወር መግቢያ ላይ ተቃውሞውን መርተዋል ተብለው የታሰሩት ሰዎች ከእስር ቤት ሳይወጡ ቤታቸው እንዲፈርስ ተደርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከማንነት ጋር በተያያዘ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የሚነሳው ጥያቄ እየጨመረ መሆኑ ታውቋል። የትግራይ ክልል መንግስት ከዚህ ቀደም የነበሩ የተለያዩ በኦሮምኛና በአማርኛ የተጻፉ ወካይ ስሞችን በመለወጥ የአካባቢውን ታሪክና ባህል ለማጥፋት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። “የራያ ህዝብ ባህልና ታሪክ ” በሚል ርእስ በክብሮም አሰፋ የተጻፈው መጽሀፍ እንዳይሰራጭ መታገዱ በአካባቢው ያለውን ውጥረት እንደሚያሳይ ነዋሪው ገልጸዋል።

አላማጣ ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት የወሎ ክፍለሀገር ግዛት እንደነበር ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ የአካባቢውን ሰዎች ለማነጋገር ጥረቶችን እያደረግን ነው እንደተሳካልን እናቀርባለን።

የአላማጣ ከተማ አስተዳዳር ጽህፈት ቤትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎችን ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም።