(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 28/2010) በአለም የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ የሼህ መሃመድ አላሙዲን ስም አለመስፈሩ ታወቀ።
ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል በአለም በሃብት ግንባር ቀደም የሆኑት ቢልጌትም በአማዞኑ ባለቤት ጄፍ ቢዞ ተበልጠው ወደ ሁለተኛ ደረጃ መውረዳቸው ተሰምቷል።
በአለም የሚገኙት ቢሊየነሮች ቁጥር 2 ሺ 208 መድረሱም ተመልክቷል።
የባለጸጎቹን የሃብት መጠን በተመለከተ አመታዊ ሪፖርቱን ያወጣው ፎርብስ መጽሔት ይፋ ባደረገው የ2018 የሃብታሞች ዝርዝር ዚምባቡዌና ሃንጋሪ ቢሊየነሮቻቸውን አስመዝግበዋል።
የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቢዞስ በባለጸጎች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 12 ዲጂት ማለትም ከመቶ ቢሊየን ዶላር በላይ ሃብት በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል።
የሃብታቸው መጠንም 112 ቢሊየን ዶላር ሆኗል።
የማይክሮሶፍቱ የረጅም አመታት 1ኛ ቢሊየነር ቢልጌት በ90 ቢሊየን ዶላር ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ብለዋል።
በ84 ቢሊየን ዶላር የሶስተኝነቱን ደረጃ የያዙት ዋረን በፌት ናቸው።
ሶስቱም አሜሪካውያን ሲሆኑ በ4ኝነት ደረጃ የተቀመጡት ፈረንሳዊው በርናርድ አርኖልት የ72 ቢሊየን ዶላር ባለጸጋ ሆነዋል።
የፌስቡክ ፈጣሪው ወጣቱ ማርክዙክበርግ በ71 ቢሊየን ዶላር የአለማችን 5ኛ ሃብታም ሆኖ ተመዝግቧል።
በአለም ከሚገኙት 2 ሺ 208 ቢሊየነሮች 585 ቢሊየነሮችን በመያዝ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።
ቻይና 373 ቢሊየነሮችን በመያዝ ከአሜሪካ ትከተላለች።
ፎርብስ እንደዘገበው የባለጸጎቹ ጠቅላላ ሃብት 9 ነጥብ 1 ትሪሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን አምና ከነበረው በ18 በመቶ ጨምሯል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼህ መሃመድ አላሙዲን ግን ከ2ሺ 208ቱ ባለጸጎች ዝርዝር ውስጥ ስማቸው አለመኖሩን መረጃዎች አመልክተዋል።
ሆኖም ፎርብስ እንዳስታወቀው የሼህ መሃመድና የሌሎች የሳውዲ ባለሃብቶች የሃብት መጠን ምን ያህል እንደቀነሰ ስላልታወቀ በዝርዝሩ ውስጥ ታልፈዋል።
ከአፍሪካና ከመላ ጥቁሮች ግንባር ቀደም ሆነው የተገኙት ደግሞ ናይጄሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ ናቸው።
በአለም ላይ ያላቸው ደረጃም 100ኛ ሲሆን የሃብታቸው መጠንም 14 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ከአለም ሃብታሞች የ766ኛ ደረጃ ይዘዋል።
ስልጣን ከያዙ ወዲህም ሃብታቸው መቀነሱ ታውቋል።