መጋቢት ፳፯( ሃያ ሰባት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኖርዌይ የዜና አገልግሎት በምህጻረ ቃሉ ኤን አር ኬ እንደዘገበው ለፓርላማው የሚቀርበው ረቂቅ ፤ የስደተኞች ጉዳይ በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኝ ሆኖም የመኖሪያ ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች እንዲታሰሩ የሚደነግግ ነው።
በግራ እና የዲሞክራቲክ ፓርቲ የተዘጋጀው ይህ ረቂቅ ወደ ፓርላማው ለመመራት በቂ ድጋፍ ማግኘቱ ተመልክቷል። ረቂቁ ከጸደቀ ፖሊስ ለማመልከቻቸው በቶሎ ምላሽ አግኝተው ህጋዊ የመኖሪያ ወረቀት ያላገኙ ስደተኞችን የማሰር ሥልጣን እንደሚኖረው-የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ሲልቪ ሊስታውግ መናገራቸውን ኤን አር ኬ ዘግቧል።ረቂቅ ሰነዱ ማክሰኞ በኖርዌይ ፓርላማ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል። በኖርዌይ ከ800 በላይ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውን እንደሚገኙ ይታወቃል።
ይህ ረቂቅ ከመውጣቱ በፊት የኖርዌይ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ኢትዮጰያውያኑን በግዳጅ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያኑ በበኩላቸው ይህን የኖርዌይ መንግስትን ውሳኔ እየተቃወሙ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ ሊያጋጥማቸው የሚችለው አደጋ የከፋ መሆኑን በመግለጽ የኖርዌይ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያደረገውን ስምምነት እየተቃወሙ ባለበት ወቅት የዚህ ዓይነት ረቂቅ ተዘጋጅቶ ወደ ፓርላማ መመራቱ እጅግ እንዳሣሰባቸው በመጥቀስ፤ የሰብ ዓዊ መብት ተሟጋቾችና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድምጻቸውን እንዲያሰሙላቸው ጥሪ አቅርበዋል።