በናይጀሪያ አቡጃ የሚገኝ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንዲዘጋ ለጊዜው ቢወሰንም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአማራጭነት ተጠቃሚ ነው ተባለ

ኢሳት (የካቲት 28 ፥ 2009)

በናይጀሪያ አቡጃ ከተማ የሚገኝ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ለጊዜው እንዲዘጋ ቢወሰንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአማራጭነት የቀረበን አየር ማረሪያ ለመጠቀም ብቸኛ አየር መንገድ ሆኖ መቅረቡን የናይጀሪያ የአቪየሽን ባለስልጣናት አስታወቁ።

በአቡጃ ከተማ የሚገኘው የናምዲ አዚክዌ አየር ማረፊያ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ወደ ከተማዋ አለም አቀፍ የበረራ አገልግሎትን የሚሰጡ 25 አየር መንገዶች በአማራጭነት የቀረበውን አየር ማረፊያ በመቃወም በረራ እንደማያደርጉ ይፋ አድረገዋል።

የሃገሪቱ ባለስልጣናት ያቀረበው አማራጭ አየር ማረፊያ አለም አቀፍ ደረጃ የጠበቀ አይደለም በማለት ሉፍታንሳ አየር መንገድን ጨምሮ ወደ አቡጃ ይበሩ የነበሩ አየር መንገዶች በሙሉ በረራን እንደማያደርጉ አቋም በመውሰዳቸው ዘ-ሰን የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

የአቡጃ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለጊዚያዊነት እንዲዘጋ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ወደ ከተማው የሚጓዙ አለም አቀፍ መንገደኞች በሌጎስ እንዲያርፉ አሊያም በሃርኮርት ወደብ አርፈው በተሽከርካሪ አሊያም በባቡር ወደ አቡጃ እንዲጓዝዙ አማራጭ መቅረቡ ታውቋል።

የናይጀሪያ የአቪየሽን ሚኒስትር ሃዲ ሲርካ የሃገራቸው መንግስት በረራ ለማቋረጥ ከወሰኑ አየር መንገዶች ጋር ድርድር ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

በአማራጭነት የቀረበው አየር ማረፊያም የጸጥታውም ሆነ የማኮብኮቢያ መንገድ አለም አቀፍ ደረጃ የጠበቀ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ከአለም አቀፍ አየር መንገዶች የቅረበውን ቅሬታ ለማሳመን መሞከራቸውን ዘ-ሰን ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።

በአቡጃ የሚገኘው አለም አቀፍ አውሮፓን ማረፊያ ለስድስት ሳምንታት ብቻ እንደሚዘጋ የተናገሩት ሃላፈው የደንበኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል መንግስት የጥንቃቄ ዝግጅት ማድረጉን አክለው ገልጸዋል።

ይሁንና የሉፍታንሳ፣ የቱርክ እንዲሁም የሌሎች አለም አቀፍ የአየር መንገዶች በማራጭነት የቀረበው ጊዜያዊ አየር ማረፊያ አለም አቀፍ ደርጃውን የጠበቀ አይደለም በማለት ሰኞ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም በረራ እንደማያደርጉ ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይጀሪያ ብዙ መንገደኞችን የሚያጓጉዝ ሲሆን በምን ሁኔታ በብቸኝነት አማራጩን ለመጠቀም ፈቃደኛ እንደሆነ የሰጠው ምላሽ የለም።