በነጻነት ሃይሎች እና በህወሃት/ኢህአዴግ  ወታደሮች መካከል የሚካሄደው ውጊያ እንደቀጠለ ነው

ኅዳር ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :-በዳባት ወረዳ ድልድይና መንደርጌ አካባቢ በህዝብ በሚደገፉ የነጻነት ሃይሎችና በህወሃት/ኢህአዴግ ወታደሮች መካከል የተጀመረው ውጊያ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን፣ በአገዛዙ ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ህዝብ ሙሉ በመሉ ድጋፉን እየሰጠ ባለው ጦርነት ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ የአገዛዙ ወታደሮች መገደላቸውንና የጦር መሳሪያዎችን መማረካቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

በርካታ ወታደሮችን የጫኑ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደ ሰሜን እያቀኑ ሲሆን ፣ ገዢው ፓርቲ ጠረፋማ የሰሜን ከተሞችን መቆጣጠር እየተሳነው መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች እና መኮንኖች በቅርቡ አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል። ምንጮች እንደገለጹት 11 የሚሆኑ የሩስያ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች በመኮንኖች ክበብ ከኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ከወታደራዊ አዛዦች ጋር ተገናኝተዋል።

አብራሪዎቹ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በአብራሪነት ተቀጥረው ለማገልገል ተቀጥረው ሳይመጡ እንዳልቀረ ምንጮች ገልጸዋል።