ነሀሴ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአዲስ አበባ እና አካባቢው ሙስሊም ማህበረሰብ በቅርቡ በፌደራል ፖሊስ እና በደህንነት ሀይሎች በማእከላዊ እስር ቤት በቁጥጥር ስር የዋሉ የኢትዮጵያ ሙስሊም ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ለማስፈታት የነገውን የኢድ አል ፈጥር በአል የአዲስ አበባ ስታዲዮምን ስግደት ሊጠቀሙበት መዘጋጀታቸውን ምንጮቻችን ገልጠዋል።
የታሰሩ ወገኖቻችንን ሳናስፈታ ወደ ቤታችን አንገባም የሚል መሪ ቃል መዘጋጀቱም ታውቋል።
በትናንትናው የጁመአ ጸሎት አብዛኛው ሙስሊም ወደ አንዋር መስጊድ ሄዶ በመንግስት ካድሬ መጅሊስ እና ኢማም ሼህ ጠሀ ሞሀመድ ሀሩን አሰጋጅነት ከመስገድ መታቀቡ ይታወሳል።
ሰሞኑን የአዲስ አበባ ሙስሊሞች በ ሞባይል ኤስ ኤም ኤስ፣ በኢንተርኔት እና በፌስ ቡክ የሚያደርጉትን የመረጃ ልውውጥ ለማስቆም ኢትዮቴልኮም ኔትወርክ በማጥፋትና በማሳጠር ለማወክ እየሞከረ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጧል።
በነገው እለት ለሚደረገው ተቃውሞ የተለያዩ መስጊዶች ህዝቡን እያስተባበሩት ሲሆን፣ አዲሱ ሚካኤል አካባቢ የሚገኘው ፍትህ መስጊድ ኢማም ሲያስተምሩ አካባቢው ሲቪል በለበሱ ፖሊሶች ተከቦ ነበር።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ በቋሚነት በአወልያ መስጊድ ከተጀመረ 10 ወራት ያሳለፈ ሲሆን ፣ የአህባሽን አስተምሮ መንግስት በላያችን ላይ አይጭንብንም፣ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የሆኑ የመጅሊስ አመራሮች ይውረዱ፣ አወልያ ነጻ በሆነ የሙስሊም ኮሚቴ ይመራ፣ የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው ይታወሳል።
____________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide