(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 19/2010)
በነቀምቴ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄደ። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮች ለሰዓታት ታግተው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተከትሎ በተነሳ የህዝብ ተቃውሞ የአገዛዙ ታጣቂዎች ህዝቡ ላይ ሲተኩ የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቋል።
ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ አልወጣም። ደጋፊዎቻቸውን ለማግኘት ወደ ወለጋ ያመሩት የኦፌክ አመራሮች አስቸኳይ አዋጁን የሚጥስ ተግባር ነው በሚል በፌደራል ፖሊስ ጉዛቸውን እንዲያቋርጡ ተደርገዋል። በደምቢዶሎ በሳምንቱ መጨረሻ በአገዛዙ ታጣቂዎች በተወሰደ እርምጃ የሰው ህይወት ማለፉም ታውቋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ/ኦፌኮ/አመራሮች በነቀምቴ ከተማ ከታገቱ በኋላ ከሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ በኮማንድ ፖስቱ በመከልከላቸው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
በዚህ ምክንያት የተበሳጩት የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ስታዲየም ውስጥ ሲጠባበቁ ቆይተው የኦፌኮ መሪዎች መከልከላቸውን ሲያውቁ አገዛዙን በመቃወም ወደ አደባባይ ወጥተዋል።
በቅርብ ከእስር የተለቀቁት የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና እና ተቀዳሚ ምክትላቸው አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም ሌሎች አመራሮች ከሕዝቡ ጋር አልተገናኙም።
ጉዳዩ በሰላም እንዲጠናቀቅ አመራሮቹ ወደ አዲስ አበባ ቢመለሱም የነቀምቴ ነዋሪዎች ግን ከአገዛዙ ታጣቂዎች ጋር ተጋጭተዋል።በከተማዋ ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ እንደነበር በቪዲዮ የተሰራጨው መረጃ ያስረዳል።ስለደረሰው ጉዳት ግን የተገለጸ ነገር የለም።
በደምቢዶሎ ግን 7 ሰዎች ከዚሁ ግጭት ጋር ተያይዞ መቁሰላቸውን የኦፌኮ ምክትል ሊቀመነበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ተናግረዋል።አቶ ሙላቱ ገመቹ እንዳሉት ስብሰባው የተከለከለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ነው።ሕዝቡ ግን አዋጁን ከምንም ባለመቁጠር አደባባይ መውጣቱ ነው የተነገረው።
እንደ አቶ ሙላቱ ገለጻ የኦፌኮ አመራሮች ከአምቦ እስከ ነቀምቴ የሕዝብ አቀባበል እየተደረገላቸው ነቀምቴ ሲደርሱ ክልከላ ተደርጎባቸዋል።እናም በተለያዩ የምስራቅ ወለጋ ከተሞች ሊያደርጉ የነበረውን ጉዞ መሰረዛቸውን አቶ ሙላቱ ገልጸዋል።