በነቀምቴ ከተማ ሁለት የአጋዚ ወታደሮች ሲገደሉ ሌላ አንድ መቁሰሉ ተነገረ

ኢሳት (ጳጉሜ 1 ፥ 2008)

በምዕራብ ኦሮሚያ ክልል ስር በምትገኘው የነቀምቴ ከተማ ማክሰኞ ምሽት ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በፈጸሙት የቦንብ ጥቃት ሁለት የአጋዚ ወታደሮች መገደላቸውንና ሌላ አንድ ወታደር መጎዳቱን እማኞች ለኢሳት ገለጹ። ወተደሮቹ ትቃቱ የተፈጸመባቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ወከባ ማድረሳቸው አስመርሯቸው እንደሆነ ተመልክቷል።

ወታደሮቹ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በከተማዋ ቀበሌ 07 ውስጥ በሚገኝ አንድ የመንግስት ድርጅት ውስጥ መከሰቱን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

በመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ላይ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት ተከትሎ የአጋዚ ወታደሮች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ፣ ከጥቃቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሶስት የወለጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መገደላቸውን የሟቾችን ስም በመግለጽ እማኞች ለኢሳት አስታውቀዋል።

በከተማ የስራ ማቆም አድማ በመካሄድ ላይ መሆኑን የተናገሩት የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች፣ ግድያ የተፈጸመባቸው ሶስቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በወለጋ የሆሮ ጉድሩ አካባቢ ነዋሪዎች ሲሆን፣ አስሬናቸው ወደ መኖሪያ ቀያቸው መሸነኘቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ለወራት በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር በሺዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል መከላከያ ሰራዊትና የአጋዚ ልዩ ሃይሎች በወለጋና የተለያዩ የክልሉ ቦታዎች ሰፍረው እንደሚገኙ ይታወቃል።

በክልሉ ተቃውሞን እያሰሙ የሚገኙ ነዋሪዎች እነዚሁ ሃይሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡና ግድያ እንዲቆም በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኦሮሚያ ክልል ለወራት ከተቀጣጠለው ተቃውሞ ጋር በተገኛኘ እስካሁን ድርስ ወደ 500 አካባቢ ሰዎች መሞታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይሁንና መንግስት በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ቢገልጽም፣ በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ስዎችን ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።