ህዳር ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት በቶሮንቶ ከተማ ላይ የተሰራው ዘመናዊው የመንበረ ብርሃን ቅድስት ማርያም ካቴድራል በብፁ አቡነ መርቆርዮስ ቅዳሜ ኖቬምበር 17 ቀን 2012 ዓም ተመርቆ ሥራውን ጀመረ።
ከተለያዩ ክፍላተ ዓለም የመጡ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናንና ካናዳውያን ባለስልጣናት በተገኙበት እሁድ ኖቬምበር 18 ቀን 2012 ዓ ም በሰፊው ቀጥሎ በዋለው የምረቃ ስነስርዓት ላይ ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ባደረጉት ንግግር የመንበረ ብርሃን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ካህናትና ምዕመናን ተባብረው የሰሩት ይህ ድንቅ ካቴድራል “ኢትዮጵያውያን አብሮ መብላት እንጅ አብሮ መስራት ኣይችሉም” የሚለውን የተሳሳተ አጉል ትችት የሰበረው መሆኑን ጠቅሰው አበው አባቶቻችንም ይህንን ድንቅ ታሪክ ሲሰሩ እንዲኖሩ አስረድተዋል። አያይዘውም ይህች ቤተክርስቲያን የምነት ቤታችን ብቻ ሳትሆን የባህላችን፣ የቋንቋችን፣ የማንነታችን መግለጫ በመሆኗ ይህ ትውልድ ተረክቦ ሊንከባከባት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከሃያ ስምንት ዓመት በፊት ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ካህን ሁነው የቤተክርስቲያን አገልግሎት በካናዳ የጀመሩት ሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ለዚህ ትልቅ ውጤት ማብቃታቸውና ዘጠኝ ለሚሆኑ በካናዳ ለተቋቋሙ አብያተ ክርስቲያናት ግንባር ቀደም ድጋፍ ሲሰጡ መኖራቸው በተለያዩ ተናጋሪዎችና ምዕመናን ምስጋናና አድናቆት ተችሯቸዋል።
በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት ካናዳውያን ባለስልጣናትና የፓርላማ አባላት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ስቲቨን ሃርፐር እንዲሁም የኦንቴርዮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶልተን ማጊንቲ የደስታ መግላጫ መላካቸውን አሳውቀው ኢትዮጵያውያን ይህን የመሰለ ድንቅ ስራ በመሥራት ለካናዳ ጊዜ የማይሽረው ታሪካዊ ስጦታ ማበርከታቸውን አድንቀው ይህን ለሠራችሁ ኢትዮጵያውያን ይህ ድንቅና ውብ ካቴድራል ምን ያህል እንደሚያኮራችሁ ቢታወቅም ባለ ብዙ ባህል ለሆነችው ካናዳ ደግሞ ውበትና ታሪክ ይጨምርላታል ብለዋል።
የቶሮንቶና ያካባቢው ምዕመናን በሁለት ዓመት ውስጥ ወጪውን የሚሸፍን ገንዘብ ከማዋጣት በላይ ኢንጂነሮች ፣የኤሌትሪክ ባለሙያዎች ፣የህንጻ ስራ ተቋራጮች፣ የኮምፒዩተር ቴክኒሻኖች፣ ሰዓሊዎች፣ የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ደከመን ሳይሉ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስና የጉልበት አስተዋጾ ማድረጋቸውን አቶ አቤል አድማሱ የሰበካ ጉባኤው ሊቀመንበር አስረድተዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፣ በውጭ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ አቡነ መልከ ጼዴቅ ፣ የኣውሮፓና የምስራቅ አፍሪካ ሊቀጳጳስ አቡነ ኤልያስ ፣ የኦንታርዮ ሊቀጳጳስ አቡነ ዲሜጥሮስ በካልጋሪ የምዕራብ ካናዳ ሊቀጳጳስ ፣አቡነ ሚካኤል ፣ አቡነ መቃርዮስ የአውስትራልያና በካናዳ የኩቤክ ሊቀጳጳስ በሁለቱም ቀናት በቡራኬው፣ በማህሌቱና፣ በቅዳሴው የተሳተፉ ሲሆን ከተለያዩ የአሜሪካና የካናዳአ ብያተክርስቲያናት የመጡ መዘምራን እንዲሁም እውቁ ኢትዮጵያዊ በገና ደርዳሪ አቶ ዓለሙ አጋ ልዩ ልዩ ዜማ በማሰማት ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተዋል።