(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 3/2010) በትግራይ ክልል ሚሊሻዎችና በአፋር አርብቶ አደሮች መካከል ግጭት መቀስቀሱ ተሰማ።
ሁለት የትግራይ ሚሊሻ አባላት በግጭቱ መገደላቸው ታውቋል።
በአፋር ክልል ኩናባ ወረዳ ዋህደስ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሱዳ በተባለ ተራራ ላይ ትላንት የተጀመረው ግጭት ዛሬም ቀጥሏል።
የትግራይ ክልል ከሚሊሺያዎች በተጨማሪ ልዩ ሃይልና መከላከያ መሰለፋቸውን የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ለኢሳት በላከው መረጃ ላይ ተመልክቷል።
በሌላ በኩል ለኤርትራ አጎራባች በሆነው ቢር ወረዳ የመከላከያ ሰራዊት ሁለት ሰዎችን መግደሉን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።
ከትግራይ ክልል ጋር አዋሳኝ የሆኑ የአፋር ወረዳዎች ግጭት ተለይቷቸው አያውቅም።
በተለይም የኮልነባ ወረዳ በየጊዜው በሚከሰት የሁለቱ ወገኖች ግጭት የተነሳ ሰላም ያጣ አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
የህወሀት አገዛዝ ወደስልጣን ከመምጣቱ በፊት ከምስረታው ጀምሮ የትግራይን ካርታ በደደቢት በረሃ ላይ ሲያዘጋጅ ከአማራና አፋር ክልሎች ሰፊ አካባቢዎች ወደ ትግራይ እንዲጠቃለል አድርጓል።
ከአማራ ወልቃይትንና ራያን ወደትግራይ ክልል እንዲካለሉ ሲደረግ ከአፋር ሰውኔ በሚል የሚጠሩ 4 ቀበሌዎች ከነዋሪው ይሁንታ ውጭ የትግራይ አካል እንዲሆኑ ተደርገዋል።
ላለፉት 17 ዓመታት የሰውኔ ቀበሌዎች እስከፌደሬሽን ምክር ቤት በመሄድ ያለፍላጎታቸው ወደ ትግራይ ክልል መጠቃለላቸውን በመጥቀስ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምላሽ አላገኙም።
የህወሀት ፍላጎት በሰውኔ ቀበሌዎች ሳያበቃ ኮልነባ የተሰኘውን የወርቅ ክምችት የሚገኝበትን ወረዳ ወደ ትግራይ ለማካለል ከፍተኛ ጫና በማድረግ ላይ ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታት ኮልነባን በሃይል ለመውሰድ የትግራይ ሚሊሻዎችና ልዩ ሃይል የአፋር አርብቶ አደሮችን በማጥቃት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
ትላንት የዚሁ የህወሀት የተስፋፊነት ህልም አካል ነው የተባለ ጥቃት በአፋር አርብቶ አደሮች ላይ ተፈጽሟል።
በኮልነባ ወረዳ ዋህደስ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሱዳ በተባለ ተራራ ላይ ግጭት እንደነበረ ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ ተመልክቷል።
የትግራይ ሚሊሺያዎች ከልዩ ሃይል ጋር ተሰልፈው የአፋርን አርብቶ አደሮች ባጠቁበት የትላንቱ ግጭት ከአፋሮች በኩል ከመቁሰል ያለፈ ጉዳት አለመድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከትግራይ ሚሊሺያዎች ሁለት መገደላቸው ታውቋል።
ግጭቱ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው የትግራይ ሚሊሺያዎችን ለማገዝ ልዩ ሃይል ተጨማሪ ወታደሮቹን ማሰማራቱ ታውቋል።
ከትግራይ ወደ ኮልነባ የተዘረጋውን የኤሊክትሪክ ሃይል እንዲቋረጥ በመደረጉ በአካባቢው ኢንተርኔትን ጨምሮ ሁሉም ዓይነት ግንኙነቶች መቋረጣቸውን ነው የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ያስታወቀው።
ይህም በአካባቢው እየተካሄደ ያለውን ግጭት በተመለከተ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ እንዳደረገውም ድርጅቱ ገልጿል። በትግራይ ክልል በኩል ስለግጭቱ የተባለ ነገር የለም።
በሌላ በኩልም ለኤርትራ ወሰን ቅርብ በሆነችው ቢር ወረዳ ሁለት ሰዎች በመከላከያ ሰራዊቱ መገደላቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ግድያው ለምን እንደተፈጸመ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በኮማንድ ፖስቱ አማካኝነት የተፈጸመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
6 የአፋር ክልል ወረዳዎች ከትግራይ የሚዋሰኑ ሲሆን በተፈጥሮአዊ ሀብታቸው የተነሳ የህወሀት አገዛዝ በየጊዜው የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት የሃይል ርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል።
በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ነው የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ለኢሳት ባደረሰው መረጃ ላይ የተመለከተው።