በትግራይና አማራ ድንበር አካባቢ የተነሳውን ግጭት እንዲያዩ ከተመረጡት የኮሚቴ አባላት መካከል አንደኛው በድጋሜ ታፈኑ

ጥር ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ እና በትግራይ ድንበር አካባቢ አወዛጋቢ ከሆኑት ቦታዎች መካከል አንዱ የሆነውንና የትግራይ ክልል የእኔ ነው በማለት ወደ ክልሉ እንዲገባ የሚጠይቀውን ግጨው እየተባለ የሚጠራውን ቦታ ሁኔታ ለማየት ከተመረጡት የኮሚቴ አባላት መካከል አቶ ዋኘው ደሳለኝ ጥር 26 ቀን 2009 ዓም ማክሰኚት ላይ በድጋሜ በህወሃት የደህንነት አባላት ታፍነው ተወስደዋል። ግለሰቡ ያሉበት ቦታ እስካሁን አልታወቀም።
ኢህአዴግ ችግሩን ሁለቱ ክልሎች ተነጋግረው ይፍቱት የሚል ውሳኔ ካሳለፈ በሁዋላ፣ የብአዴን ሊ/መንበር እና ም/ል ጠ/ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ በረከት ስምዖን፣ ካሳ ተክለብርሃንና አለምነው መኮንን በተገኙበት የጠገዴ የወረዳ አመራሮችና የብአዴን አባላት የሆኑት አቶ ደምለው ጀጃው፣ አቶ ዋኘው ደሳለኝ እና አቶ ተሻገር መለሰ ተመርጠው ነበር። ተመራጮቹ የወረዳ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ የብአዴን አባላትም ሲሆኑ፣ ህወሃትም 3 የድርጅቱን አባላት ተወካይ አድርጎ በመላክ ውይይት ቢጀመርም፣ የብአዴን ተወካዮች የህወሃት ተወካዮች የያዙትን አቋም በመቃወማቸው በትግራይ የደህንነት ክፍል ወከባ ሲደርስባቸው ቆይቷል።
የብአዴን ተወካዮች ችግራቸውን ለብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ቢያሳውቁም፣ አቶ አለምነው ግን “ ተስማምታችሁ ስሩ፣ ችግሮች ቢኖሩም አንዳንድ ጊዜ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት ተመልከቱት፣ ህወሃትን እንደጠላት አትዩት፣ በአጋርነትና በእህት ድርጅትነት እዩት “ የሚል መልስ ሰጥተዋቸዋል።
የብአዴን ተወካዮች የህወሃትን ሴራ ማጋለጣቸውን በመቀጠላቸው መስከረም 25 ቀን 2009 ዓም አቶ ዋኘው ደስአለኝና አቶ ተሻገር መለሰ በምእራብ ዞን አስተዳዳሪ በአቶ ኢሳያስ ታደሰ ትእዛዝ ፣ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ተወካይ በሆኑት አቶ አሸናፊ ተስፋሁንና አቶ ይዘዝ ተሾመ አማካኝነት በመከላከያ አባላት ቁጥጥር ስር ውለው፣ በአዘዞ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ድብደባና ሌሎችም አሰቃቂ ድርጊቶች ተፈጽሞባቸዋል።
ተወካዮቹ የደረሰባቸውን ግፍ ለብአዴን ቢያሳውቁም ጉዳዩ በፌደራል ደረጃ የተያዘ ነው በማለት የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች መልስ የሰጡ ሲሆን፣ ህወሃትን ፍላጎት አናስፈጽምም ያሉት ሁለቱ የኮሚቴ አባላት ወደ ብርሸለቆ ተልከዋል።
ተወካዮቹ ጥር 26 ቀን 2009 ዓም ከብርሸለቆ እስር ቤት ተፈትተው ወደ ጎንደር ሲያመሩ ማክሰኝት ከተማ ላይ በሽፍን መኪና ይከታተሉዋቸው በነበሩ የደህንነት ሰራተኞች ከመኪና እንዲወርዱ ተደርጎ፣ አቶ ዋኘው ደሳለኝን አፍነው ወስደውታል።
ሌላው የኮሚቴ አባል የሆነው አቶ ደምለው ጀጃው ጥር 18 ቀን 2009 ዓ/ም ምሽት ላይ በደህንነት አባላቱ ትእዛዝ ከቤታቸው ታፍነው ከተወሰዱ 11ኛ ቀን አልፎአቸዋል። ግለሰቡ ያሉበት አድራሻ እስካሁን አልታወቀም።
የብአዴን ተወካዮች ታፍነው ከተወሰዱ በሁዋላ የህወሃት ወኪሎች ብቻቸውን እንደፈለጉ ድንበሩን እያሰመሩ ነው። የብአዴን አመራሮች ጥያቄ ሲቀርብላቸው፣ ኮማንድ ፖስቱን ጠይቁ በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።