ሰኔ 14 ፥ 2009
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አማካኝነት በባህርዳር ከነማና በሽሬ እንደስላሴ ቡድን እንዲሁም በመቀሌ ከነማና በአማራ ውሃ ሥራዎች መካከል በባህርዳር ሊካሄድ የታቀደው ጨዋታ ላልታወቀ ጊዜ መራዘሙን ፌደሬሽን አስታወቀ። በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የአማራ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ ቢሮዎች ጨዋታው ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር መጠየቃቸውንም ማክሰኞ ፌደሬሽኑ ሰኔ 13/ 2009 በፃፈው ደብዳቤ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ሰኔ 13/ 2009 በፃፈው ደብዳቤ አማራ ውሃ ሥራዎች ከመቀሌ ከነማ እንዲሁም ሽሬ እንደሥላሴ ከባህርዳር ከነማ በባህርዳር ከተማ እንዲያካሒዱት የታቀደው የእግር ኳስ ጨዋታ ወደአልታወቀ ስፍራ ላልታወቀ ጊዜ መራዘሙን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የጨዋታውን ቦታ ለመለወጥና ጊዜውን ለማራዘም የወሰነው ከአማራ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች በቀረበለት ጥያቄ መሆኑን አመልክቷል። የአማራ ክልል የተለያዩ ቢሮዎች ከፌደሬሽኑ ጋር በየትኛው የግንኙነታቸው መሥመር ጠየቁ የሚለው ጥያቄ ደብዳቤውን ተከትሎ እየተነሣ ቢሆንም ምላሽ አልተገኘም። ፌደሬሽኑ በደብዳቤው እንደገለፀው የአማራ ክልል ቢሮዎች ጨዋታው ከባህርዳር ይልቅ በአዲስ አበባ እንዲካሔድ ጠይቀዋል። ሆኖም ግጥሚያው እንደሚካሄድ ያልወሰነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጨዋታው የሚካሄድበትን መርሐግብር አላስቀመጠም።
የፌደሬሽኑ ደብዳቤ ከመውጣቱ በፊት ከትግራይ ወደ ባህርዳር የሚመጡት ክለቦች የደህንነት ዋስትና ጥያቄ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሣል።
ግንቦት 6 ፥ 2009 ዓም በባህርዳር ከነማና በመቀሌ ከነማ መካከል በመቀሌ ከተማ የተካሔደው የእግር ኳስ ውድድር ግጭት ማስከተሉ ሲታወስ፣ ይህንን ግጭት ተከትሎ የመጣው ውጥረት እስካሁን አልበረደም።