ኢሳት ዜና:- ተማሪ አስቻለው በቡታጅራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚማርበት ጊዜ ገዢው ፓርቲ ተማሪዎችን ለአባልነት ለመመልመል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመቃወም፣ እንዲሁም በመሬትና በተዛማጅ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ዙሪያ ጥያቄዎችን በማቅረቡ ተከሶ ለአንድ አመት በእስር እንዲቀጣ ተፈርዶበት ነበር።
ተማሪ አስቻለው ለኢሳት እንደገለጠው የገዢው ፓርቲ አባል የሆኑት ርእሰ መምህርና መምህራን አስቻለው የሚያቀርባቸውን ጥአቄዎችም ሆነ ከተማሪዎች ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት አይወዱለትም ነበር።
በ2002 ዓም ደግሞ ተማሪ አስቻለው ማትሪክ ለመፈተን በሚዘጋጅበት ጊዜ ከፍተኛ ውጥረት ስለበዛበት ማቁዋረጡን ገልጦ፣ ምርጫ 2002 ከተጠናቀቀ በሁዋላ ውጥረቱ ሊቀንስ ይችላል በሚል ተስፋ ትምህርት መጀመሩን ይገልጣል።
ይሁን እንጅ ኢህአዴግ አሁንም ተማሪዎችን ለመመልመል የሚያድረገውን ጥረት ባለማቆሙ ግጭት ውስጥ መግባቱን ይናገራል። ተማሪ አስቻለው ስብሰባውን ለቅቆ በሚወጣበት ጊዜ በርእሳነ መምህራኑ አማካኝነት መታሰሩን ይገልጣል።
ተማሪ አስቻለው ከታሰረ በሁዋላ በ7 ወንጀሎች መከሰሱን ይገልጣል ። በ2003 ዓም ክፍል ውስጥ የመሬት ፖሊሲን በተመለከተ የጠየቀው ጥያቄ እንደ አንድ ክስ ሆኖ መቅረቡን
ተማሪ አስቻለው ይናገራል።
ተማሪ አስቻለው ከአንድ አመት የስቃይ እስር በሁዋላ መፈታቱን ገልጦ ፣ በአሁኑ ጊዜ ቀድሞ ይማርበት በነበረው ትምህርት ቤት አትመዘገብም በመባሉ ወደ ሌላ አካባቢ ተዘዋውሮ ለመማር መገደዱን ገልጧል።
ኢሳት የተማሪ አስቻለውን ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆዬቱ ይታወሳል። ገዢው ፓርቲ ትምህርት ቤቶችን ወደ ካድሬ ማፍሪያነት በመለወጡ የትምህርት ጥራት በእጅጉ እንዲያሽቆለቁል ማድረጉን ተቃዋሚዎችና ምሁራን በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወቃል።