በቴፒ ወታደሮች ሴቶችን አስገድደው ይደፍራሉ ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ

ጥቅምት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪዎች እንዳሉት ሰላም እና መረጋጋት እናመጣለን በማለት የሰፈሩት ወታደሮች፣ ህዝቡን አለመረጋጋት ውስጥ እየከተቱት መሆኑን ይናገራሉ።
በአካባቢው የሰፈሩት ወታደሮች ሴቶችን አስገድደው ይደፍራሉ የሚሉት ነዋሪዎች፣ ሴቶች ወደ ምንጭ ወርደው ውሃ መቅዳት አልቻሉም ይላሉ።
ባለትዳር ሴቶች ሳይቀር እየተደፈሩ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በተለይ በቆርጫ ህብረት በሚባል ቀበሌ ወታደሮች በእናቶች ላይ ዘግናኝ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን በምሬት ይገልጻሉ። ቆርጫ ቀበሌ ባለፈው ሳምንት በቴፒ ወጣቶች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በተደረገ የተኩስ ለውውጥ በርካታ ወታደሮች የተገደሉት ቦታ ነው።
በአካባቢው ያለው ውጥረትና ወከባ አለመቆሙን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። የወጣቶች ምክትል አዛዥ፣ ከወታደሮች የሚደርሰውን ጫና በመፍራት ትግላችንን አናቆምም ሲል ለኢሳት ተናግሯል።