ኢሳት (የካቲት 20 ፥ 2009)
ቅዳሜ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር በህንድ ለማረፍ ተገዶ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአንድ ቀን መዘግየት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱን የህንድ የአቪየሽን ባለስልጣናት ገለጹ።
255 መንገደኞችን እና የበረራ ባለሙያዎችን ይዞ ከሙምባይ ወደ ካትማንዱ ከተማ በማቅናት ላይ እንዳለ ፓይለቱ (የአውሮፕላኑ አብራሪ) የቴከኒክ ችግር እንዳጋጠመውና ለማረፍ መገደዱን ለትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሪፖርት ማድረጉን ኢንዲያ ቱዴይ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ET8806 የሚል የበረራ መለያ ቁጥር ያለው ይኸው የመንገደኞች አውሮፕላን በካትማንዱ ከተማ ባረፈ ጊዜ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ከፍተኛ የጥንቃቄ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር ተመልክቷል።
ይሁንና በ245 መንገደኞችና በ10 የበረራ ባልደርቦች ላይ ምንም አይነት ችግር ሳይፈጠር አውሮፕላኑ በሰላም ማረፉንና ለረጅም ሰዓታት የፈጀ የቴክኒክ አገልግሎት መካሄዱን ጋዜጣው ምንጮችን ዋቢ በማድረግ አስነብቧል።
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ይኸው የመንገደኞች አውሮፕላን በእስራኤል በኩል በማድረግ ሰኞ ምሽት አዲስ አበባ እንደሚገባ የአቪየሽን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በህዳር ወር መጨረሻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞት በፓኪስታን የላሆር አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ አርፎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በግድ ለማረፍ ስለተገደደው የመንገደኞች አውሮፕላን የሰጠው ምላሽ የለም።