ሚያዚያ ፳፩(ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል ልዩ ልዩ ከተሞች በቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያዎች ና ጽህፈት ቤቶች የሚተዳደሩት በርካታ የንግድ ሸዶች ከስራ ፈላጊ ወጣቶች ይልቅ ባለሃብቶች እንዲጠቀሙባቸው መደረጉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ስራ ፈላጊ ወጣቶች ገልጸዋል፡፡
“አመራሮችን በተከታታይ ብንጠይቅም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም” የሚሉት ስራ ፈላጊ ወጣቶች “በተለይ በመንገድ ፊት ለፊትና ለንግድ አመች የሆኑ ቦታዎችን ለባለሃብቶች በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ አግባብ አይደለም” በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
በተለያዩ ህዝባዊ ውይይቶች ጉዳዩን በህዝብ ፊት ቢያቀርቡም ምላሽ እንዳላገኙ የሚናገሩት ወጣቶች፤በርካታ ምሩቃን የመስሪያ ቦታ አጥተው ያለ ስራ በተቀመጡበት ሁኔታ፤የገዢው መንግስት አመራሮች ግን የመስሪያ ሸዶችን በጥቅማ ጥቅም በመደለል ለባለሃብቶች መስጠታቸውን አሁንም አለማቆማቸው እንዳስከፋቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎች አክለውም “አመራሮች የሰሩትን የመልካም አስተዳደርና ክራይ ሰብሳቢነት ችግር በልዩ ልዩ ህዝባዊ ስብሰባዎች ህብረተሰቡ ባቀረበባቸው ግልጽ መረጃ ከሃላፊነት የተነሱ አመራሮች አሉ” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች “አመራሮቹ ሲነሱም ሆነ ተመልሰው ሌላ መስሪያ ቤት ሲሾሙ ህብረተሰቡ እውቅና የለውም”በማለት ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን “አመራሮቹ ችግር ከፈጠሩበት መስሪያቤት ተነስተው ያለምንም ውድድር ሌላ ቦታ በአመራር ደረጃ መመደባቸው አግባብ አይደለም” ይላሉ፡፡
በአንድ የወረዳ ከተማ ብቻ በዲግሪና በዲፕሎማ የተመረቁ ከ500 በላይ ስራ ፈላጊ ወጣቶች እያሉ ፤አንዳንዶች ያለምንም ማስታወቂያና ውድድር በቀጥታ ተመድበው ሲሰሩ መታየታቸው ስራ ፈላጊ ወጣቶች በገዢው መንግስት ተስፋ እንዲቆርጡ እንዳደረጋቸው በመናገር ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሚዲያውን በመጠቀም “የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እፈታለሁ” በማለት የገዢው መንግስት የሚያደርገው ሩጫ በህብረተሰቡ ላይ የሚፈጸሙ በርካታ ያልተሰሙ የአስተዳደር በደሎችን በማሰማት የስርዓቱን ማንነት ከማሳየት ውጭ የሰጠው ፋይዳ እንደሌለ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡