በታሰሩ የፌደራል ፖሊስ ስልኮች ላይ የተገኙት የአቶ አንዳርጋቸውና የመንግስቱ ሃይለማርያም ፎቶዎች መሆናቸው ታወቀ

ሚያዝያ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ሳምንት በተወሰኑ የፊደራል ፖሊስ አባላትና እና በማረሚያ ቤቶች ጠባቂዎች ላይ በተካሄደ ድንገተኛ ማጣራት፣ በ18 የፀጥታ አባላት ስልኮች ላይ በእስር ላይ የሚገኙት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና የቀድሞው

ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሃይለማርያም  ፎቶዎች መገኝታቸውን የደህንነት ምንጮች ገልጸዋል።

የደህንነት ሃይሉ ከባለቤቱ ፈቃድ ውጭ ስልክ የመጥለፍ ፤ የኢንተርኔት አካውንት በመስበር መረጃ የመስረቅና መረጃ የማዛባት ፣ እንዲሁም የግል ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ላይ ፍተሻ የማድረግ ስልጣን እንዳለው  እንዲሁም የፀጥታና የደህንነት አባላት ከአሸባሪዎች ጋር

ግንኙነት አላቸው ፤ በሀገሪቱ ለውጥና ነውጥ እንዲመጣ የሚደረገውን ትግል ይደግፋሉ የሚል የግምገማ ድምዳሜ በደህንነቱ በኩል ከተያዘ በኃላ ምርመራ መጀመሩን ምንጮች ተናግረዋል።

ግምገማውን ተከትሎ በአዲስ አበባ የፊደራል ፖሊስ እና የቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች የፀጥታ አካላት ስልኮች ላይ ፍተሻ መደረጉን ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል።

ፖሊሶቹ በማእከላዊ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው ነው። በፌደራል ፖሊስ አባላትና በአዛዦች መካከል ያለው አለመግባባት እየሰፋ መሄዱንም መረጃዎች አመልክተዋል።

ከምርጫው ጋር ተያይዞ በጭንቀት ውስጥ ያለው መንግስት የፀጥታ ሃይሉን ክህደት ፤ የህዝቡን ፅኑ የለውጥ ፍላጎት በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሆነ እየተከታተለው መሆኑን የመረጃ ምንጮች አስተያየታቸውን አስፍረዋል።