በሶማሊያ በቅርቡ የተፈጸመውን ጥቃት ሳይጨምር ከ20 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸው ተነገረ

ዜና (ሰኔ 20 ፥ 2008)

በተያዘው አመት ብቻ ሰሞኑን በአልሸባብ የተፈጸመውን ጥቃት ሳይጨምር ከ20 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ መሞታቸውን ቢቢሲ ዘገበ።

በሚያዚያ ወር በቤይ ግዛት በደረሰ የፍንዳታ አደጋ ስድስት ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በጥር ወር 15 የኢትዮጵያ ወታደሮች በታችኛው ሸበሌ ግዛት በተካሄደ ግጭት መሞታቸውን የዜና አውታሩ አመልክቷል።

በተያዘው ወር መግቢያ ላይ በአንድ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ወደ 160 የሚደርሱ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደተገደሉ ቢቢሲ አልሻባብን ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ አውስቷል።

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ሃልጋን ተብሎ በሚጠራው ግዛት በተፈጸመው ጥቃት ምንም ወታደር እንዳልሞተበት ማስተባበያን መስጠቱን የዜና ወኪሎ አውስቷል።

በሃልጋን ግዛት የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሟች ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያ መንግስት የሃዘን መልዕክት ማስተላለፉ ይታወሳል።

ከኢትዮጵያ ወታደሮች በተጨማሪ በተያዘው የፈረንጆቹ መጀመሪያ ወር ላይ 180 የኬንያ ወታደሮች በተመሳሳይ ጥቃት መገደላቸውን የሶማሊያውን ፕሬዚደንት ቢገልፅም የኬንያ መንግስት ቁጥሩን አስተባብሎ በጥቃቱ የሞቱ ወታደሮች ቁጥር ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።

ባለፈው አመት መስከረም ወር በጃናሌ ግዛት በተፈጸመ ጥቃት 12 የዩጋንዳ እንዲሁም በሰኔ ወር 50 የብሩንዲ ወታደሮች መገደላቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዑክ ከአውሮፓ ህብረት በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለሟች ወታደሮች 50ሺ ዶላር ካሳ ክፍያ ሲከፍል መቆየቱን ከልዑኩ ድረገጽ ከሰፈረ መረጃ ታውቋል።

ይሁንና የአውሮፓ ህብረት ለሰላም አስከባሪ ልዑክ ሲሰጥ የቆየው ድጋፍ እንዲቀንስ መወሰኑ በሰላም አስከባሪ ቡድኑ ተልዕኮ ላይ ከፍተኛ ጫናን ይፈጥራል ተብሎ ተሰግቷል።

ኢትዮጵያ ከአራት ሺ የሚበልጡ ወታደሮች በሶማሊያ አሰማርታ የምትገኝ ሲሆን ከሰላም ልዑኩ በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በተጠናጠል አሰማርታ እንደምትገኝ ይታወቃል።