በተውፊቅ መስጊድ ተቃውሞ ተካሄደ

ኢሳት (መጋቢት 16 ፥ 2008)

በየሳምንቱ አርብ የሚካሄደውን የሙስሊሙ ማህበረሰብ ልዩ የጸሎት ፕሮግራም ተከትሎ አርብ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሜክሲኮ ተብሎ በሚጠራው ተውፊቅ መስጊድ ተቃውሞ ተካሄደ።

በአራተኛው ተከታታይ ሳምንት በተካሄደው በዚሁ ተቃውሞ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ይደርስብኛል ያሉትን ብሄራዊ ጭቆና በማውገዝ የተለያዩ መፈክሮችን ሲያውለበልቡ ማርፈዳቸውም ታውቋል።

“ትግላችን ይቀጥላል” “ፍትህን ቀበሯት” “ኮሜቴው ይፈታ” “የነቃ ህዝብን ያሸነፈ አፈና የለም” የሚሉ መፈክሮችን ሲያውለበልቡ የነበሩት የሙስሊሙ ማህበረሰብ በእስር ላይ የሚገኙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

በከተማዋ በሚገኙ የተለያያዩ መስጊዶች ተቃውሞኣቸውን እያቀረቡ የሚገኙት እነዚሁ አካላት መንግስት ለጥያቄያቸው ምላሽን ካልሰጠ ተቃውሞው ቀጣይ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል በማለት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሶስት አመት በፊት ጀምሮ ተከታታይ ተቃውሞዎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎም በርካታ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ የፍትህ ሚኒስቴር ከወራት በፊት አምስቱን በምህረት መፍታቱ የሚታወቅ ነው።

ይሁንና፣ ተቃውሞአቸውን ቀጥለው የሚገኙት የሙስሊሙ ማህበረሰብ በእስር ላይ የሚገኙ ከ10 የሚበልጡ የኮሚቴው አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና መንግስት በሃይማኖቱ ላይ ያደርገዋል የሚሉትን ጣልቃገብነት እንዲያቆም ጠይቀዋል።

አርብ ተውፊቅ መስጊድ በተካሄደው ተቃውሞ እነዚሁን ጥያቄዎች የሚያስተጋቡ መፈክሮች ሲውለበለቡ ማርፈዳቸውን ከሃገር ቤት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።