ታህሳስ ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በደቡብ ወሎ በተውለደሬ ወረዳ አቶ አበራ ካሳ የተባሉ ጠበቃ ከቀበሌው ሊቀመንበር ጋር በመሬት ጉዳይ ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ክርክር በፍርድ ቤት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ፣ ሊቀመንበሩ ደጋፊዎቻቸውን አስተባብረው ጠበቃው እንዲደበደቡ አድርገዋል፡፡ ጠበቃውም በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ሆስፒታል ገብተዋል።
የመሬቱ ባለቤት አቶ አስፋው ሽበሺ የሚባሉ አርሶአደር ሲሆኑ ፣ የቀበሌው 01 እና 02 ሊቀመንበሮች መሬቱን ለግላቸው ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ ነበር።
የቀበሌ ሊቀመንበሮቹ ትናንት ምሽት ላይ የአርሶአደር ሽበሺን ቤት ያቃጠሉባቸው ሲሆን፣ የጠበቃው ባለቤት ደግሞ ዛሬ ቤታቸውን ለቀው ካልወጡ ቤታቸው እንደሚቃጠልባቸው ተነግሮአቸው ቤታቸውን መልቀቃቸው ታውቋል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ በተወልደሬ ወረዳ የቀበሌ ባለስልጣናቱ መንግስት እንደሌለ አድርገው እንደሚቆጥሩና ህብረተሰቡን እንደሚያሰቃዩ ተናግረዋል።