የካቲት ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የገዳሙ ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት ከወልቃይት ተነስቶ በዋልድባ አብረንታት ገዳም አድርጎ ወደ ማይፀብሪ የሚሰራው መንገድ በ2004ዓ/ም በገዳሙ ፣በአካባቢው ሕብረተሰብ እና በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጠንካራ ተቃውሞ የተነሳ ተቋርጦ ቆይቷል።
መንግስት ወደ ገዳሙ የሚገባው ለአፈር ምርምር እንጂ መንገድ ለመስራት አይደለም በሚል የመንግስት ካድሬዎችና አንዳንድ መነኮሳትና የቤተክነት ሃላፊዎች የሀሰት ምስክርነት እንዲሰጡ አድርጎ ህዝቡን ካዘናጋና “ገዳሙ አይታረስም ብለው የሚቃወሙትን ጠንካራ መነኮሳት” ከገዳሙ ካስወጣ በሗላ፣ አሁን የመንገድ ስራውን እንደገና መጀመሩን ተናግረዋል።
የመንገድ ስራው የዛሬ 3 አመት ገደማ በወልቃይት በኩል የዛሪማን ወንዝ አቋርጦ ከገዳሙ ክልል በመግባት ማይ ደርሆት ከተባለው ቦታ ድረስ ደርሶ የቆመ ቢመስልም፣ አሁን እንደገና ከማይፀብሪ ተነስቶ በአዳበስ ከተማ አቋርጦ ከገዳሙ አፋፍ እንስያ ወንዝ መድረሱንም መነኮሳቱ ገልጸዋል።
መንግስት መነኮሳቱን ለማስፈቀድ በሚል በጥር ወር ማይፀብሪ ከተማ ላይ 2 ጊዜ ፣ በያዝነው ወር ማይጋበ ከተማ ላይ ደግሞ አንድ ጊዜ ሰብስቦ ያነጋገረ ቢሆንም፣ ያለስምምነት ተበትኗል።
በመነኮሳቱና ህዝቡ አቋም የተናደዱት ባለስልጣኖች “ስታስቀሩት እናያለን” በማለት በመነኮሳቱ ላይ መዛታቸውን አክለው ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የማይጸብሪን አስተዳዳሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።