በተሰጣቸው ግዳጅ የተበሳጩ የናይጀሪያ መከላከያ አባላት በአውሮፕላን ማረፊያ ለረዥም ሰዓታት በመተኮስ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።

በተሰጣቸው ግዳጅ የተበሳጩ የናይጀሪያ መከላከያ አባላት በአውሮፕላን ማረፊያ ለረዥም ሰዓታት በመተኮስ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 06 ቀን 2010 ዓ/ም ) በጸጥታ ማስከበር ሥራ ላይ የተሰማሩ የናይጀሪያ ወታደሮች በድጋሚ የተሰጣቸውን ግዳጅ በመቃወም ከትናንት እሁድ ጀምሮ ጥይት ወደላይ እየተኮሱ ነው።
የሰራዊቱ አባላት ጥይታቸውን ሽቅብ እያርከፈከፉ ያሉት በሰሜናዊቷ የናይጀሪያ ከተማ በማይዱግሪ አውሮፕላን ማረፊያ ነው። የተቃውሟቸው ምክንያትም ወደ ግንባር በመዝመት ከቦኮሀራም ሚሊሻዎች ጋር እንዲዋጉ በድጋሚ ግዳጅ መታዘዛቸው ነው።
በመሆኑም፣ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀንን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ወታደሮቹ ካማይዱግሪ – ወደ ኒጀር ድንበር አዋሳኟ እና የቦርኖ ግዛት መቀመጫ ወደሆነችው ወደ ማርቴ ከተማ ሊወስዳቸው በአውሮፕላን ማረፊያው ተዘጋጅቶ የሚጠብቃቸው አውሮፕላን ላይ ለመሳፈር አሻፈረኝ በማለት መሳሪያቸውን አውጥተው ወደ ላይ በመተኮስ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
የዓይን ምስክሮች ለሬውተርስ እንደተናገሩት የሰራዊቱ አባላት በመጀመሪያው ዙር ተቃውሟቸው ትናንት በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከ18 ሰዓት ተኩል ጀምሮ ያለማቋረጥ ለአራት ሰዓታት ያህል ወደላይ ሲተኩሱ አምሽተዋል።.
“እየተኮስን ያለነው በመቆጣታችን ነው። ለአራት ዓመታት ያህል እዚህ በግዳጅ ተሰማርተን ሳለ እንደገና ወደ ሌላ ቦታ ግዳጅ የምንላከው ለምንድነው?” ብሏል ከወታደሮቹ አንዱ በሰጠው አስተያዬትልል አክሎም፦”ቀደም ሲል ወደግዳጅ ስንሰማራ ከሰርጎ ገብ የቦኮሀራም ሚሊሻዎች ጋር እየተዋጋን የምንቆዬው – ቢበዛ ለሦስት ዓመታት ብቻ እንደሆነ ተነግሮብ ነበር”ብሏል።
የሀገሪቱ መከላከያ እስካሁን በጉዳዩ ዚሪያ የሰጠው መግለጫም ሆነ አስተያዬት የለም።