ኢሳት (ታህሳስ 14 ፥ 2009)
በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሳማንታ ፖወር መንግስት ለእስር የዳረጋቸውን ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈታ ጥሪን አቅርበዋል።
በሃገራቸው ለእስር የተዳረጉ እና በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የከፈተችውን ዘመቻ በማስተባበር ላይ የሚገኙ አምባሳደሯ ኢትዮጵያ ለእስር የዳረገቻቸውን የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የሃገሪቱ ዜጎች በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መብቶቻቸውን እንዲከበሩ አሳስበዋል።
ዛሬ ሃሙስ ለእስር ከተዳረጉ አንደኛ አመት የሞላቸውን አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ግብፅና ጋምቢያ ለእስር የዳረጓቸውን የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ አሜሪካ በዘመቻዋ ጠይቃለች።
ከአፍሪካዊያኑ ሃገራት በተጨማሪ አዘርባጃን፣ ሶሪያ ዩክሬን፣ ቤኔዝዌላ፣ ኢራን፣ ቻይናና ኩባ ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን እንዲወስዱ በመካሄድ ላይ ባለው ዘመቻ መጠቀሳቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል ተብለው ለእስር የተዳረጉት የዶ/ር መረራ ጉዲና ጉዳይ አሳስቦት እንደሚገኝና ድርጊቱ በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያን ስታወጣ የቆየችው አሜሪካ ባለፈው ሳምንት የሰብዓዊ መብት ልዑካን ወደ አዲስ አበባ በመላክ በጉዳዩ ዙሪያ ምክክር ማካሄዱም ታውቋል።