በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች የአገራችን ችግሮች በስልጠና አይፈታም አሉ

ነሃሴ ፲፬(አስራ አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ ” የመንግስትን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ለከፍተኛ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማስተዋወቅ” በሚል

የጀመረው  ስልጠና በወሎ ዩኒቨርስቲ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ተማሪዎች በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩ በርካታ ችግሮችን እያነሱ ጥያቄዎችን እየጠየቁና አስተያየቶችንም

እየሰጡ ነው።

በወሎ ዩኒቨርስቲ በመካሄድ ላይ ባለው ስልጠና ተማሪዎች ኢህአዴግ እራሱን ከቀድሞ ስርአቶች ጋር ማወዳዳሩን እንዲያቆም ጠይቀዋል። ቀድሞ ስርአቶች ያልተማሩ

በመሆናቸው ስህተት ቢሰሩ አይገርምም ያሉት ተማሪዎች፣ የእነሱን ስህተት ብቻ እያጎላችሁ የራሳችሁን  ድክመት ለመሸፈን ትሞክራላችሁ ሲሉ ወቅሰዋል።

የብሄርን ጉዳይ አስመልክቶ ደግሞ እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ብሄር ብቻ ነው ያለው እንዴ ሲሉ ጠይቀዋል። ህወሃት በአገሪቱ ያሉ ቁልፍ ቦታዎችን መቆጣጠሩን

የተቹት ተማሪዎች፣ ህወሃት በአጼ ሚኒለክ ዘመን የተፈጸሙትን ድረጊቶች እያነሳ አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት እየሰራ ነው ሲሉ ነቅፈዋል።

ከሙስሊሙና ከክርስቲያን ተማሪዎች ከፍተኛ ጥያቄ ያስነሳው የሃይማኖት ጉዳይ ሲሆን፣ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ማስገባቱን፣ የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ

የኮሚቴ አባላት ያለአገባብ መታሰራቸውን ተማሪዎች አንስተዋል።

አገር በዶክመንታሪ አይመራም የሚሉት ተማሪዎች፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎችን ማሰሩ በህዝብ ዘንድ እንዲጠላ ከማድረጉም በተጨማሪ ዋጋ ያስከፍለዋል ሲሉ

ተማሪዎች ተናግረዋል።

ኢህአዴግ ልማት አላማጣም በማለት የተናገሩ አንዳንድ ተማሪዎች፣መጣ የተባለውም ልማት ግሎባላይዜሽን ያመጣው እንጅ የኢህአዴግ ስራ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ነጻ ፕሬስ የሚባል በአገሪቱ ውስጥ እንደሌለም ተጠቅሷል። አንድ ተማሪ “ኢህአዴግ በከንቱ እየለፋ ነው ፣ ተማሪዎች ለ15 ቀናት ቀርቶ ለአንድ አመት ቢሰለጥኑ የሚለወጥ

ነገር አይኖርም” ሲል ተናግሯል።

አወያዮቹ በሃይማኖት ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሚቀጥሉት ቀናት መልስ እንደሚሰጥባቸው ተናግረዋል። ለሌሎች ጥያቄዎች የተሰጡት መልሶችም ተማሪዎችን አለማርካቱን

ተወያዮች ለኢሳት ገልጸዋል። ወይይቱ ምሽት ላይ በአንድ ለአምስት አደረጃጃት በተማሪዎች መኝታ ክፍል መቀጠሉም ታውቋል። የአንድ ለአምስት ውይይቱ ተማሪዎች

የኢህአዴግ አባል እንዲሆኑ ለማግባባት ተብሎ የሚደረግ ነው።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የሚካሄደው ውይይትም አሰልቺ መሆኑን ተማሪዎች ይገልጻሉ። ተማሪዎቹ የአኖሌን ሃውልት በአርሲ መትከል የፈለጋችሁት ህዝቡን የመከፋፈል አጀንዳ

ስላላችሁ ነው፣ ለሱዳንና ለጅቡቲ መሬት በነጻ እየሰጣችሁ ነው፣ ህዝቡ በቀን አንድ ጊዜ ለመብላት በተቸገረበት ወቅት የኢህአዴግ አባል በተቀጠረ በ2 አመታት ውስጥ ቪላ ቤት

እና መኪና ያገኛል በሚል አስተያየት አዘል ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ በመካሄድ ላይ ባለው ውይይት ደግሞ ተማሪዎች  የህዝባዊ ወያን ሃርነት ትግራይ ንብረት ስለሆነው ኢፈርት ኩባንያ ባለቤትነት ጥያቄ አንስተዋል። የመንግስት

ደርጅቶች ወደ ግል እየዞሩ ቢሆንም፣ በእጅ አዙር የሚገዙት የእናተ ባለስልጣናት ናቸው በማለት የተናገሩት ተማሪዎች፣ በቅርቡ በታሰሩት በእነ አቶ መላኩ ፋንታ ዙሪያ የህወሃቱ

ኢፈርት እጅ አለበት በማለት አስተያየት ሰጥተዋል። ኢፈርት የአገሪቱን አብዛኛውን ሃብት ጠቅልሎ መያዙን፣ ከታክስ ነጻ በሚያስገባቸው እቃዎች ዙሪያ ተቃውሞ አቀረቡት አቶ

መላኩ ፋንታ ተለይተው እንዲታሰሩ መደረጉን ተማሪዎች ተናግረዋል። ኢፈርትን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ አወያዮች መልስ ሳይሰጡ አልፈውታል።