በተለያዩ የክልል ከተሞች በተቧደኑ ወጣቶች እየተፈጸሙ ያሉ የጎዳና ላይ ፍርዶች በሕዝብ ዘንድ ስጋት እያሳደሩ መምጣታቸው ተገለጸ።

በተለያዩ የክልል ከተሞች በተቧደኑ ወጣቶች እየተፈጸሙ ያሉ የጎዳና ላይ ፍርዶች በሕዝብ ዘንድ ስጋት እያሳደሩ መምጣታቸው ተገለጸ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 06 ቀን 2010 ዓ/ም ) ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በትናንትናው ዕለት ብቻ በሻሸመኔ ከተማ አንድ ንጹህ ሰው ቦምብ ሊያፈነዳ ነበር በሚል መረጃ በወጣቶች ተዘቅዝቆ የተሰቀለ ሲሆን፣ ግለሰቡ ቦምብ አስገብቶባታል የተባለች ተሽከርካሪም እንድትቃጠል ተደርጋለች፡፤
ሆኖም የኦሮሚያ ፖሊስ ነገሩን አጣርቶ በሰጠው መግለጫ ግለሰቦ ቦምብ ይዞ ነበር የተባለው ፍጹም ስህተት መሆኑን ከማስታወቁም በላይ የተቃጠለችውም ተሽከርካሪ የመስተዳድሩ ንብረት እንደሆነች አረጋግጧል።
ነገሩ እውነት ቢሆን እንኳ አንድ ወንጀለኛ ሲያዝ ለህግ አስከባሪዎች አሳልፎ በመስጠትር ፋንታ ወጣቱ የዚያ አይነት የጎዳና ላይ ፍርድ መስጠቱ ፣እንኳን በህግ አግባብ-በምንም የሞራል አመክንዮ ትክክል ሊሆን አይችልም ያሉ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ድርጊቱን አጥብቀው ኮንነዋል።
በስፍራው ተሰማርተው የነበሩ ጸጥታ አስከባሪዎችስ አንድ ሰው ተዘቅዝቆ እስኪሰቀል ድረስ ምን እየሰሩ ነበር? በማለት የጠየቁት ታዛቢዎች፣ ወንጀሉን ከፈጸሙት ወጣቶች በተጨማሪ የዜጎችን ደህንነት እንዲጠብቁ በስፍራው ተመድበው ሳሉ ነገሩን በዝምታ የተመለከቱ ፖሊሶችም ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል በቡድን የተደራጁ የጎንደር ወጣቶችም በትናንትናው ዕለት የጫት ነጋዴዎችን ጫት በመውረስ በእሳት ማቃጠላቸውን ከምስል ጋር ተያይዞ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ጫት በወጣቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር ትውልድን የሚያደነዝዝ ዕፅ ቢሆንም፣ የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ መንግስት በህግ ባልከለከሉበት ሁኔታ የለፍቶ አዳሪ ነጋዴዎችን ቅሪት ቀምቶ ማቃጠል ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ያሉት የህግ ባለሙያዎች፣ በዚህ ረገድ የወጣቱና የአክቲቪስቱ ተግባር ሊሆን የሚገባው ወጣቱ ከጫት እንዲርቅ ማስተማር እና ማንቃት ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።
በአንዳንድ የክልል ከተሞች ደግሞ በቡድን የተደራጁ ወጣቶች ኮንዶሚኒየም ቤት እና መሬት ድረስ እስከማከፋፈል መድረሳቸው ተመልክቷል።
እንዲህ ያሉ በጎዳና ላይ የሚፈጸሙ የቡድን ፍርዶች ወዳለፉት አስከፊ ስርዓቶች እንዳይመልሱን እየሰጋን ነው ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይ ለለውጡ አስተዋጽኦ ያደረገው ወጣት ከመስመር እንዳያፈነግጥና ድርሻውንና ኃላፊነቱን አውቆ በተሰመረው የህግ መስመር በአግባቡ እንዲሄድ፣ ከወዲሁ በተደጋጋሚ ሊነገረው ይገባል ብለዋል።
ይሁንና ከሁሉም በላይ ይህን ክፍተት እያሰፋው የመጣው፣ መንግስት ህግ በማስከበር በኩል ያሳየው መለሳለስ መሆኑን መካድ አይቻልም የሚሉት የህግ ባለሙያዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቻ እየተፈጸሙ ባሉ ወንጀሎች ፍትህ ሢሰጥ አለመታዬቱ፣ ሕዝብን በራሱ መንገድ እርምጃ እንዲወስድ እንደሚያስገድደው ሊጤን ይገባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።