በተለያዩ የኦሮሚያ ኣካባቢዎች የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 11/2009)  ከእለት ገቢ ግምት ትመና ጋር ተያይዞ ባለፈው ሳምንት የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ በአምቦ ፥ ወሊሶ፥ ጊንጪ፥ ባኮ፥ ግንደበረት እና ነቀምት እንደቀጠለ የኢሳት ምንጭች ገልጸዋል ።

በወሊሶ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን የንግድ መደብሮች ፥ ሱቆች የተለያዩ ድርጅቶችና ኣገልግሎት መስጫ ተቋማት ዝግ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በኣምቦ ከተማ የስራ ማቆም አድማው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ህዝቡ ከነጋዴው ጋር በመሰለፍ የተጣለውን ግብር እየተቃወመ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

በነቀምት ከተማ የአድማ ጥሪ የያዙ ወረቀቶች በሰፊው እየተበተኑ ይገኛሉ።

ከተማዋ በከፍተኛ ውጥረት ላይ እንደሆነችም ለማወቅ ተችሏል።

የኦሮሚያ ክልል ቃል-አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ በአንቦ የተነሳውን ተቃውሞ አምነው መንስኤው”በከተማዋ ከእለት ገቢ ትመና ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች ቅሬታ ያቀረቡበት መንገድ ትንሽ ለየት ያለ በመሆኑ እንጂ የጎላ የፀጥታ ችግር የለም” በማለት አስተባብለዋል።

አቶ አዲሱ እንደገለፁት በአብዛኛው የተፈጠረው ችግር የግንዛቤ ክፍተት በመሆኑ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።