መስከረም ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶችና መንግስት በጋራ በፈረንጆች አቆጣጠር ሴፕቴምበር 24 ፣ 2015 ያደረጉት ስብሰባ ቃለ ጉባኤ እንደሚያስረዳው ፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች እጅግ አሳሳቢ የሆነ የውሃና የምግብ እጥረት ተከስቷል። ችግሩም በሚቀጥሉት ሁለት ወራት እንደሚጨምር ለኢሳት የደረሰው ቃለ ጉባኤ ያስረዳል። በተለይ በሶማሊ ክልል ባለው የጸጥታ ሁኔታ አስቸኳይ ምግብና ውሃ ለማቅረብ እንዳልተቻለ ሪፖርቱ ይጠቅሳል። እርዳታ ለመስጠት የመከላከያ ሰራዊት ፈቃድ መጠየቅ እንዳለበትም በቃለጉባኤው ላይ ሰፍሯል።
በኦሮምያ፣ በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ የሚገኙ 37 ወረዳዎች በከፍተኛ የውሃ እጥረት የተጠቀሱ ሲሆን፣ ውሃ በቦቴ ለማዳረስ የተደረገው ሙከራም አጥጋቢ አይደለም ተብሎአል። በአማራ ክልልም እንዲሁ ደቡብና ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ጎንደር እና ምስራቅ ጎጃም ከፍተኛ የውሃ እጥረት አጋጥሟቸዋል። በትግራይ፣ በደቡብ ምስራቅ፣ እና ማእከላዊ ዞኖች፣ በአፋር 11 ወረዳዎች እንዲሁም በሲቲ፣ ሃርሺንና ኖጎብ ዞኖች የውሃ እጥረቱ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ዩኒሴፍ ከክልል መሪዎች ጋር በመተባባር አደጋው የሚቀንስበትን መንገድ እያፈላለገ መሆኑ በቃለጉበኤው ተጠቅሷል።
አሳሳቢ የምግብ እጥረት ከታየባቸው ክልሎች መካከል ደግሞ በአፋር ክልል ዞን 1፣ 2 እና 5፣ በሶማሊ ክልል ሲቲ እና ፋን ፋን፣ ዞኖች፣ በአማራ ክልል፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋግ ሂምራና ምስራቅ ጎጃም ፣ በኦሮምያ በምስራቅና ምእራብ ሃረርጌ፣ አርሲ፣ ቦረናና ምስራቅ ሸዋ፣ በደቡብ ክልል ሲዳማ፣ ፣ ሃድያ፣ እና ወላይታ ዞኖች እንዲሁም በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን ይጠቀሳሉ።
በእነዚህ ወረዳዎች ትምህርት ቤቶች አሁንም የተዘጉ ሲሆን፣ ዩኒሴፍ ለህጻናቱ ባሉበት ቦታ ትምህርት የሚሰጥበትን መንገድ እያፈላለገ ነው።
የአለም የምግብ ድርጅት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እስካሁን 31 ሺ ሜትሪክ ቶን እህል የረዳ ሲሆን፣ በጅቡቲ ወደብ የሚገኘው የእርዳታ እህል ባፋጣኝ ካልገባ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችል የአለም የእርዳታ ድርጅቶች አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጽያ መንግስት ላጋጠመው ድርቅ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቂ የዕርዳታ ምላሽ እያገኘ አለመሆኑን ባለፈው ሳምንት የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማረጋገጣቸው የሚታወስ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ለተከሰተው ድርቅ የሚውል ወደ 237 ሚሊየን ዶላር ወይም ወደ 5 ቢሊዮን ብር ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን እስካሁን የፌዴራል መንግስት 700 ሚሊየን ብር፣ የኦሮሚያ መንግስት 500 ሚሊየን ብር ከመደጎማቸው በስተቀር የተገኘ ድጋፍ የለም፡፡
መንግስት ለ2008 በጀት ዓመት በጠቅላላው 223 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ዓመታዊ በጀት የያዘ ሲሆን ከዚህ በጀት ውስጥ 28 ቢሊየን ብር ገደማ የበጀት ጉድለት ያለበት በመሆኑ ይህንን ጉድለት ከሀገር ውስጥና ከውጪ ከሚገኝ ብድርና ዕርዳታ ለመሸፈን አቅዶ በሚንቀሳቀስበት በዚህ ወቅት ፣ የድርቁ መከሰት ከባድ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ሊከተለው እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ተናግረዋል፡፡