በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች መጠነ ሰፊ ግድያ በመንግስት ሃይሎች መፈጸሙ ታወቀ

ኢሳት (ነሃሴ 2 ፥ 2008)

ባልፉት ሶስት ቀናት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ በፈጸሙት የተኩስ ዕርምጃ ከ50 የሚበልጡ ሰዎች በኦሮሞያና አማራ ክልሎች መገደላቸውን በሃገር ውስጥ የሚታተመው አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት ያሰባሰባቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ ሰኞ ዘገበ።

በተለይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ስር በሚገኙት አሳሳ፣ አዳባ፣ ሻሰማኔና ኮፈሌ ከተሞች መጠነ ሰፊ ግድያ መፈጸሙን መጽሄቱ እማኞችን በመጥቀስ አስነብቧል።

እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ በአምቦና ጊንጪ ከተሞች የጸጥታ ሃይሎች የሃይል ዕርምጃ መውሰዳቸውን ያወሳው መጽሄቱ ቅዳሜ ብቻ በክልሉ በትንሹ 30 ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል።

ከሟቾቹ በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በጥይት ተኩስ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ለእስር መዳረጋቸውንና የገቡበት የማይታወቅ ነዋሪዎች መኖራቸውን አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት በዘገባው አስፍሯል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የጸጥታ ሃይሎች በጎንደር እና ባህር ዳር ከተሞች ላይ በፈጸሙት የተኩስ ዕርምጃ ከ20 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን ያስነበበው መጽሄቱ ተጨማሪ ሰዎችን በጥይት ተኩስ ጉዳት እንደደረሰባቸው አክሎ ዘግቧል።

የመንግስት ባለስልጣናት የጸጥታ ሃይሎች ህገወጥ የተባለውን ሰልፍ ለመቆጣጠር እርምጃን እንዲወስዱ ቢገልጽም እስከ አሁን ድረስ በሰዎች ላይ ስለደረሰ ጉዳት የሰጡት መረጃ የለም።

በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎች በተለያዩ ከተሞች የቤት ለቤት ፍተሻ በመካሄድ ላይ መሆኑንና በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል ለወራት በዘለቀው ተቃውሞ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ማስታወቁ ይታወሳል።