የካቲት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመረጃ ምንጮቻችን ከተለያዩ ከተሞች የላኩልን መረጃ እንደሚያሳያው በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች መካከል የደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ሸዋ ሮቢት፣ አጣዬ፣ ቆቦ፣ ከምሴ፣ መርሳ ሾፌሮች አድማውን አጠናክረው በመቀጠላቸው፣የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል። በኦሮምያ ደግሞ በነቀምቴ ተመሳሳይ አድማ በመካሄድ ላይ ነው።
በወልድያ የተጀመረው አድማ ለሁለት ቀናት ከተካሄደ በሁዋላ ብዙዎች ታርጋቸው ተመልሶላቸው ስራ ጀምረዋል።የወረዳው ባለስልጣናት ሹፌሮቹ ያነሱዋቸውን ችግሮች እንደሚፈቱላቸው ቃል በገቡት መሰረት ስራ መጀመራቸውን የአካባቢው ወኪላችን ገልጿል።
በመርሳና ውርጌሳ አድማው የቀጠለ ሲሆን፣ በውርጌሳ መንገድ ትራፊክ ፖሊሶች ሹፌሮች መንገደኞችን እንዲጭኑ ሲያስገድዱ ውለዋል። በአካባቢው በሚገኙ መንገዶች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌደራል ፖሊስ ተሰማርቶ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ነው።
በደሴ እና ሌሎች ቦታዎች ግን በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር እስከ ምሽቱ 11 ሰኣት ድረስ አድማው ቀጥሎአል። በባህርዳርም ተመሳሳይ አድማ ለመጀመር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
በወለጋ ነቀምት ከተማም አድማው መቀጠሉን ታውቋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ ታክሲዎች ባለፈው ሳምንት መግቢያ ላይ አድማ ካደረጉ በሁዋላ፣ በወሊሶና አምቦ መስመሮችም ተመሳሳይ አድማ ሲካሄድ ቆይቷል።