በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተደረጉ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ/ም ) የራያ እና ወልቃይት የማንነት ጥያቄ እንዲከበር፣ በጣና ሐይቅንና የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስያናትን እንታደግ በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ትዕይንተ ህዝብ ተደረገ።
ካለ ህዝብ ውሳኔ ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉት ወልቃይቶችና ራያዎች ማንነታቸው እንዲከበር፣ ሰብዓዊ መብታቸውን የሚጥሱ የትግራይ ክልል ልዩ ጦር አባላት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ሲሉ ሰልፈኞቹ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ታላቁ ሃይቅ የሆነው ጣና ሃይቅን የወረረውን እንቦጭ የማጥፋት ዘመቻ በመንግስትና በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል። በተጨማሪም የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስያናትን ህልውና ጊዜ የማይሰጠው ስለሆነ የክልሉና የፌደራል መንግስት ቅርሱን ለመታደግ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
ሰላማዊ ሰልፉ ደብረ ብርሐን ከተማ፣ በወልድያ ከተማ፣ በደብረ ታቦር፣ በደሴ፣ በባህር ዳር እንዲሁም በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የ7 ቤት አገው ፈረሰኛ ማኅበር በፈረስ በታጀበ ሰልፍ መል እክቶቻቸውን አስተላልፈው በሰላም ተጠናቋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ የሚመራው የመንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በጎንደር እና በላሊበላ ጉብኝት አካሂዷል።
በጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ የሚመራው የመንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ወደ ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ አቅንተዋል። በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ ከሰፈሩት የኢትዮጵያ መለያ የሆነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ያጋጠመውን የመፍረስ አደጋም በአካል ተገኝተው ጎብኝተዋል። የልዑካን ቡድኑ በላሊበላ ከተማ በድንገት ተገኝተው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በቅርሱ ሁለንተናዊ ይዞታ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ህልውና መታደግ የመንግስትና የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑን አሳስበዋል። ”ላሊበላን የሚያክል ድንቅ የዓለምና የአፍሪካ ቅርስ ሲሆን፤ ለእኛ ደግሞ ከዚያም በላይ መኩሪያችንና መመኪያችንን ስለሆነ ደግመን መገንባት ባንችልም እንኳ መጠበቅ ግን ግዴታችን ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ በአጽንኦት ተናግረዋል።
ከጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ጋር በመሆን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ያካተተ እንደነበር የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ፍጹም አረጋ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ የአውሮፓ ጉብኝታቸውን በይፋ ጀምረዋል። በዛሬው ዕለት ከፈረንሳዩ ርዕሰ ብሄር አማኑኤል ማክሮን ጋር ተገናኝተዋል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትሩ ረቡዕ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በመገኘት ከኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።