በተለያዩ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ውጊያዎች በመካሄድ ላይ ናቸው

ኅዳር ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ዛሬ በአብድራፊ አንገረብ ወንዝ አካባቢ ራሳቸውን ባደራጁ የነጻነት ሃይሎች እና በገዢው ፓርቲ ወታደሮች መካከል ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዷል።

ዛሬ ሲካሄድ በዋለው ውጊያ በነጻነት ሃይሎችም ሆነ በገዢው ፓርቲ ወታደሮች ላይ ስለደረሰው ጉዳት የታወቀ ነገር የለም።

በሌላ በኩል በወልቃይት ትርካንና ማይነብሪ አካባቢ በአርበኞች ግንቦት7 ወታደሮችና በመንግስት ታጣቂዎች መካከል መለስተኛ ውጊያ ተካሂዷል። አንድ የግንባሩ ወታደራዊ አመራር እንደገለጹት ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ለማለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ ተመሳሳይ ግጭቶት ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም ተመሳሳይ ጦርነት ተካሂዶ፣ አባሎቻቸው ሰብረው ወደ አሰቡበት ቦታ ተንቀሳቅሰዋል ።

በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት አዲጎሹ ላይ በተደረገው የተኩስ ለውውጥ የተሰው 4 የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትን የአካባቢው ህዝብ በክብር በዋልድባ ገዳም እንደቀበራቸው ታውቋል። በአካባቢው የሚገኝ አንድ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተል ታጋይ እንዳለው ፣ የህዝቡ ድርጊት ህዝባችን ምን ያክል ፍትህ እንደተጠማና ለሚመጣው ሃይል ያለውንም  አክብሮት ያሳየበት ነው ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አገዛዙ የሚፈጽመውን ግፍ በመቃወም ወደ ጫካ የወጡ  የነጻነት ታጋዮች በአንድ ላይ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል። ታጋዮቹ በአንድ እዝ ስር በመሆን ትግላቸውን በጋራ ለማካሄድ ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ዘመናዊ የውትድርና ስልጠና ትምህርት በመውሰድ ላይ  መሆናቸውም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።