በተለያዩ ከተሞች የኮሌራ በሽታ ተከስቶ እንደሚገኝ ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 11 ፥ 2008)

በአዲስ አበባ ከተማ በመሰራጨት ላይ ያለው የኮሌራ በሽታ በመቀሌ ከተማም መከሰቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ረቡዕ አስታወቀ።

በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ተከስቷል በተባለው በዚሁ በሽታ አምስት ሰዎች ምልክቱ ተገኝቶባቸው በህክምና ላይ መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በሰኔ ወር በአዲስ አበባ ከተማ ስርጭቱን የጀመረው ይኸው የኮሌራ በሽታ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ጉዳትን እያደረሰ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የመለክታል።

የበሽታውን ስርጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በትንሹ ስድስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ከ 3ሺ የሚበልጡ ነዋሪዎች በበሽታው መያዛቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው በከተማዋ ያለው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሰዎች የተበከለ ወንዝ ውሃ እንዲጠቀሙ በማስገደዱ የበሽታውን ስርጭት ሊቀንስ አለመቻሉን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በሽታውን ለመቆጣጠር ሲደረግ የቆየው ጥረት ውጤት አለማስገኘቱን በመግለጽ ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ በማሳሰብ ላይ ይገኛል።

የኮሌራ በሽታ ስርጭቱ ከተጠበቀው በላይ በመዛመት ላይ መሆኑን ተከትሎ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የግንዛቤን ማስጨበጫ ትምህርት በዘመቻ መልክ እያካሄዱ መሆኑን ታውቋል።

ይሁንና ነዋሪዎችን በመዲናቱ ያለው የንጹህ ውሃ አቅርቦት ሊቀረፍ ባለመቻሉ በሽታው ጉዳትን እያደረሰ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ በሽታው እያደረሰ ያለውን አጠቃላይ ጉዳት መግለጽ በነዋሪው ላይ ፍራቻን ያሳድራል ተብሎ በመታመኑ መረጃ ለህዝብ ይፋ እንዳይደረግ መወሰኑን አስታውቋል።

ከሁለት ወር በፊት በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች በሚገኙ ሁለት ዞኖች ውስጥ ብቻ በትንሹ 19 ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በሽታ መሞታቸው ይታወሳል።