በተለያዩ ከተሞችና ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 4/2010)

በተለያዩ ከተሞችና ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞዎች ሲደረጉ መዋላቸው ተገለጸ።
የአጋዚ ሰራዊት ዛሬም ግድያ ፈጽሟል። ህዝቡ ደግሞ በአምቦ ሁለት የአጋዚ ወታደሮችን መግደሉ ታውቋል።
በጨለንቆ ከትላንት በስቲያ የተደረገውን ጭፍጨፋ በመቃወም በበርካታ ከተሞች ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።
በሰሜን ወሎ ኡርጌሳ ትላንት የጀመረው ተቃውሞ ቀጥሎ 3 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ህዝቡ በቁጣ አንድ ከባድ ተሽከርካሪ መሰባበሩ ታውቋል።
በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ የአጋዚ ሰራዊት ተማሪዎች ላይ በመተኮስ ግድያ መፈጸሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲም ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በሸኖ ሰሜን ሸዋ መንገድ ተዘግቷል።
ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ዛሬ ተቀላቅሏል። ባህርዳር ተጥናክሯል። ደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ግድያ ተፈጽሟል።
ጎንደር የተማሪው ተቃውሞ የሚቆም አልሆነም። ወልዲያ ዩኒቨርስቲ ህዝቡ ከተማሪው ጎን ተሰልፏል። አምቦ ሁለት የአጋዚ ወታደሮች ተገድለዋል።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከትላንት በስትያ ምሽት በተገደሉ ሁለት ተማሪዎች የተነሳ ከፍተኛ ውጥረት ተከስቷል።
በጅማ ዩኒቨርስቲ የምግብ አድማ ተመቷል። በሰሜን ወሎ ውርጌሳ ደግሞ የአጋዚ ወታደሮች 3 ወጣቶችን ገድለዋል። ሸኖ መንገድ ተዘግቷል።
የጨለንቆው ጭፍጨፋ በመላ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ቁጣ ቀስቅሷል። እዚህም እዚያም የአጋዚ ወታደር ተማሪዎችንና ህዝብን በመደብደብና በመግደል ላይ ናቸው።
ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ዛሬ ተቃውሞውን ሲቀላቀል በአዲግራት ዩኒቨርስቲ በአማራና ኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ መሆኑ ታውቋል።
ለቀናት በውጥረት የሰነበተው የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ዛሬ ከአጋዚ ሰራዊት ጋር በተፈጠረ ግጭት ወደ ተቃውሞ የተሸጋጋረ ሲሆን የአጋዚ ሰራዊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን አፍሶ ወደአልታወቀ ቦታ መወሰዱ ተገልጿል።
ባህርዳር ትላንት ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ የተሰማ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ።

 


በይባብ ግቢ አራት ተማሪዎች በአጋዚ ወታደሮች ከፎቅ ተጥለው ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሆስፒታል ገብተዋል።
ዛሬ ዩኒቨርስቲው መምህራንና ሰራተኞች ከግቢው ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአምቦ የአጋዚ ወታደሮችና የኦሮሚያ ፖሊስ ተጋጭተው ሁለት የአጋዚ ወታደሮች መገደላቸው ታውቋል።
በአጋዚ ታጣቂ አንድ ልጅ በጥይት መምታቱ ባስቆጣቸውና የኦሮሚያ ፖሊስና በአጋዚ ሰራዊት መሃል በተፈጠረው የተኩስ ልውውጥ አጋዚዎቹ እንደተገደሉ ከአካባቢው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በአምቦ ዩኒቨርስቲ የተነሳውን ተቃውሞ ህዝቡ የተቀላቀለው ሲሆን መንገዶች መዘጋታቸው ተገልጿል።
በጨለንቆ ከትላንት በስቲያ በተገደሉት 20 ሰዎች የተነሳ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሆን በአብዛኛው የምስራቅ ሀረርጌ ከተሞች የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ተቃውሞ ሲገልጹ መዋላቸው ታውቋል።
በጪናክሰን፣ አሰቦት፣ መሰላ ዞን፣ በበዴሳ፣ በጭሮ፣ የሁለተኛና አንደኛ ደረጃ እንዲሁም የዩኒቨርስቲና ኮሌጅ ተማሪዎች ከቄሮዎች ጋር በመሆን ተቃውሞ ማሰማታቸው የተገለጸ ሲሆን የንግድ እንቅስቃሴና የትራንፖርት አገልግሎት ተቋርጦ መዋሉን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በሰሜን ሸዋ ሸኖ ከተማም ተቃውሞ ሲደረግ ውሏል። ከደብረ ብርሃን ወደ ሸኖ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱንና ተሽከርካሪዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
በሰሜን ወሎ ኡርጌሳ ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት በአካባቢው ሲካሄድ የቆየው ተቃውሞ ዛሬ “ የታሰሩ ወገኖቻችን ይፈቱ” በሚል እንደገና ተቀስቅሷል።
ከኡርጌሳና ከውጫሌ የተሰባሰቡ ወጣቶች መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሟቸውን ሲገለጹ የዋሉ ሲሆን፣ ወታደሮች ከ100 በላይ ወጣቶችን ይዘው ያሰሩ ሲሆን፣ 3 ወጣቶችን ደግሞ ገድለዋል።
ከ40 በላይ ወጣቶችም ቆስለዋል። አንድ ለስላሳ መጠጦችን የጫነ መኪናም በድንጋይ ተመቷል።
አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜናም ከወልዲያ አቅራቢያ መቄት አካባቢ አንድ እንጨት የጫነ ከባድ ተሽከርካሪ በህዝቡ በተወሰደበት ርምጃ መቃጠሉ ታውቋል።
ተሽከርካሪው ደን በመጨፍጨፍ ጣውላ ወደትግራይ የሚያጓጉዝ ነው በሚል ርምጃ እንደተወሰደበት ተገልጿል።
በአጠቃላይ በመላው ሀገሪቱ የተነሳው ተቃውሞ በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል። ሁኔታው ያሰጋት አሜሪካ ማሳሰቢያ አውጥታለች።
የአሜሪካን የቀድሞ ከፍተኛ ዲፕሎማት በአስቸኳይ ጉባዔ እንዲጠራ ሀሳብ አቅርበዋል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተቀምጧል። በኢትዮጵያ ነገሮች እየተካረሩ መምጣታቸው ብዙዎችን ስጋት ላይ ጥሏል።