በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈጠረው አደጋ የሟቾች ቁጥር 72 መድረሱ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 5 ፥2009)

በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተፈጠረው አደጋ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ማክሰኞ ምሽት ድረስ ቁጥሩ 72 መድረሱ ተገለጸ። በአካባቢው በሚደረገው ፍለጋ ለአራተኛ ቀን ቀጥሎ የሚገኝ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ሊሄድ እንደሚችል የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው። ከአደጋው የተረፉ ሰዎች በቆሻሻ ክምሩ አቅራቢያ ወደ 300 የሚደርሱ ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ይገልጸዋል።

ይሁንና የነዋሪዎቹ ትክክለኛ ቁጥሩ በአግባቡ ባለመታወቁ የገቡበት ያልታወቁ ነዋሪዎችን ቁጥር ማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ የሃዘን ቀን አውጇል። በነዚሁ ቀናት በሃገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ሃገር በሚገኙ ተቋማት የሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬድዮ (ኢሳት) ሰኞ ተመሳሳይ የሶስት ቀን ሃዘን ማወጁ ይታወሳል።