በተለምዶ “ቆሼ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቁፋሮ የሚገኝ አስከሬን መጨመሩን ተከትሎ ሰዎች ወደቦታው እንዳይገቡ ታገዱ

ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2009)

በአዲስ ከተማ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነውና በተለምዶ “ቆሼ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በየዕለቱ በቁፋሮ የሚገኝ አስከሬን መጨመሩን ተከትሎ ሰዎች ወደቦታው እንዳይገቡ ታገዱ።

የቤተሰብ አባሎቻቸው የገቡበት ያልታወቁ የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ቁፋሮን የማካሄዱ ስራ ተጓትቷል በማለት ቅሬታን እያቀረቡ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። በዚሁ ድርጊት ቁጣቸውን እየገለጹ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች አደጋው ወደ ደረሰበት ስፍራ ለመጓዝ ቢሞክሩም የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እገዳን ጥለዋል።

ይሁንና የቤተሰብ አባሎቻቸው አስከሬን ማግኘት የቻሉና ከአደጋው የተረፉ ሰዎች በበኩላቸው ራሳቸው ለቁፋሮ ስራ ክፍያ መፈጸማቸውን ለመገናኛ ብዙሃን እየገለጹ ይገኛል። “እየረዳን ያለ አካል ባለመኖሩ ቁፋሮን ራሳችን እያከናወን እንገኛለን” ሲሉ የቤተሰብ አባላቸውን አስከሬን በመፈለግ ላይ የነበሩት አቶ ካሌብ ጸጋዬ የተባሉ ነዋሪ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ሌሎች ከአደጋው የተረፉ ነዋሪዎች ተመሳሳይ ቅሬታን እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን፣ ድርጊቱ በጸጥታ ሃይሎችና ቅሬታ ባደረባቸው የተጎጂ ቤተሰብ ዘንድ ውጥረት መቀስቀሱን አሶሼይትን ፕሬስ ዘግቧል።

አደጋው የደረሰበት አካባቢ ሰዎች እንዳይገቡ መደረጉን የሟቾችን ቁጥር በአግባቡ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደሚያደርገውና እገዳው ሆን ተብሎ በመንግስት የተወሰደ አሳዛኝ ዕርምጃ መሆኑን ረቡዕ ድረስ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች አስታውቀዋል።

በርካታ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አደጋው በደረሰበት ስፍራ እንዲሰማሩ የተደረገ ሲሆን፣ ወደ አካባቢው እንዳይገቡ የተደረጉ ሰዎች ዕርምጃውን በመቃወም ጥያቄን እያቀረቡ እንደሆነም ከሃገር ቤት የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ትናንት ማክሰኞ ብቻ 17 አስከሬን ከቁፋሮ መውጣቱን እና አስከሬን መለየት ባለመቻሉ ሟቾች በአፋጣኝ የቀብር ስነ-ስርዓታቸው እንዲፈጸም መደረጉን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የፖሊስ አባላት ለዜና አውታሩ አስረድተዋል። የሟቾች ቁጥር ከ80 መብለጡ ቢረጋገጥም አሁንም ድረስ ከቁፋሮ ያልወጡ ሰዎች መኖራቸው ታውቋል።

ቅዳሜ ምሽት አደጋው በደረሰ ጊዜ በትንሹ 49 ቤቶች የወደሙ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤቶቹ በአማካይ ሰባት የቤተሰብ አባላት ይኖሩ እንደነበር ነዋሪዎችን ገልጸዋል።

ይሁንና የከተማዋ አስተዳደር የወደሙትን ቤቶች ቁጥር ቢገልጽም ምን ያህል ሰው በአካባቢው ይኖር እንደነበር የሰጠው መረጃ የለም። ከአደጋው የተረፉ እንዲሁም አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት ለደረሰው አደጋ ሃላፊነት መውሰድ እንዳለበትና ተጠያቄ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለአደጋው ተጠያቄ የሆኑ ባለስልጣናት ለፍትህ እንዲቀርቡ የተጠየቁት እነዚሁ አካላት መንግስት አደጋው ከመድረሱ በፊት ዕርምጃ መውሰድ ይችል እንደነበር ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው በስፍራው ለባዮ-ፊውል የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ግንባታ ሲካሄድ የነበረው መሬት የመደልደል ስራ በቆሻሻ ክምሩ ላይ ጫናን በማሳደር እንዲደረመስ ማድረጉን ተናግረዋል። በቆሻሻ ክምሩ ወስጥ ያሉ ሰዎችን የማፈላለጉ ስራ ረቡዕ ለአምስተኛ ቀን መቀጠሉና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።