ሚያዚያ ፲፩(አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በትናንትናው እለት የቦስተን ታሪካዊ የማራቶን ሩጫ ውድድር ላይ በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያዊያውን ሯጮች አመርቂ ድል አስመዘገቡ።
በወንዶች የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያዊው ለሚ ብርሃኑ ኃይሌ በቀዳሚነት ሲገባ ርቀቱን ለመጨረስ 2:12:45 ሰከንድ ፈጅቶበታል።
ለሚን በመከተል ኢትዮጵያዊው ያለፈው ዓመት ባለድል ሌሊሳ ዴሲሳ 2:13:32 በሆነ ሰዓት በ47 ሰከንድ ተቀድሞ ሁለተኛ ሲወጣ ሌላው የአገሩ ልጅ የማነ አድሃን ፀጋዬ 2:14:02 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ወጥቷል። ኢትዮጵያዊን ሯጮች አረንጓዴ ጎርፎቹ ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ተቆጣጥረውታል።
በተመሳሳይ የእንስቶች የማራቶን ሩጫ አፀደ ባይሳ ተሰማ በአንደኝነት ስታጠናቅቅ የፈጀባት ጊዜ 2:29:19 ሲሆን እሷን በመከተል የአገርዋ ልጅ ትርፌ ፀጋዬ 2:30:03 ሁለተኛ,ስትወጣ ኬንያዋ ጆይስ ችፕኩሪ ደግሞ 2:30:50 በሆነ ሰዓት በሶስተኝነት ውድድሯን አጠናቃለች።
የቦስተን ማራቶን ከተጀመረበት እ.ኤ.ኤ 1897 ከዛሬ 120 ዓመታት ወዲህ በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያዊያን ሯጮች ድል ሲቀናቸው የመጀመሪያ ጊዜያቸው ሆኖ በታሪክ ማኅደር ስማቸው ሰፍሯል።