በቦሌ ወረገኑ የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ እርምጃ ቀጥሏል ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 17 ፥ 2008)

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረገኑ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተጀመረው ህገወጥ የተባሉ መኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ እርምጃ መቀጠሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ነዋሪዎቹ መኖሪያ ቤታቸው እንዳይፈርስባቸው ያደረጉትን ተቃውሞ ተከትሎ ወደ 200 አካባቢ ለእስር ተዳርገው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም ፖሊስ ገልጿል።

ህገወጥ ናቸው ተብለው በመፍረስ ላይ ባሉት ስፍራዎች ላይ የመከላከያ ሚኒስቴር በ450 ሄክታር መሬት ላይ የጎልፍ መጫወቻን የሚገነባ ሲሆን፣ መናፈሻና ሌሎች ግንባታዎች ይከናወናሉ ተብሏል።

ህገወጥ ግንባታ ተካሄዶባቸዋል በተባለው የወረገኑ አካባቢ የመንግስት ባለስልጣናትና የጸጥታ ሃይሎች ህገወጥ ይዞታ መያዛቸውንም ነዋሪዎችን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

በወረዳ 12 በመካሄድ ላይ ካለው የማፍረስ ዘመቻ በተጨማሪም በወረዳ 10 እና 11 የሚገኙ ህገወጥ የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችም በቀጣዩ እንደሚፈርሱ የቦሌ ክፍለከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት አስናቀ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።