ግንቦት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በወረዳ 12 የተጀመረውን የቤት ማፍረስ ተከትሎ የታሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ቦሌ ክፍለከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እየተሰቃዩ መሆኑን የአይን እማኞች ገልጸዋል። ወላጆቻቸውን ለመጠየቅ ወደ እስር ቤቱ የሄዱት ህጻናት፣ መጠየቅ አትችሉም በመባላቸው ሲያለቅሱ መመልከታቸውን የአይን እማኞች አክለው ገልጸዋል።
የመንግስት ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ ባደረሱት ጥቃት ከ8 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል። ቤት የማፍረሱ ዘመቻ ዛሬም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ወደ አካባቢው የተንቀሳቀሰው ወኪላችን በፖሊሶች እንዲመለስ ተደርጓል። አካባቢው በሙሉ በወታደሮች በመታጠሩ ወደ ውስጥ ገብቶ ፎቶ ለመቅርጽም ሆነ ሰዎችን ለማነጋገር በፍጹም አይቻልም ብሎአል።