(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 14/2011) በቅርቡ በባህርዳር ይካሄዳል ከተባለው የብአዴን ጉባኤ በፊት በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
በድርጅቱ ስራአስፈጻሚ አባላት መካከል ከፍተኛ አለመተማመንና አለመግባባት መፈጠሩን ከአካባቢው ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በብአዴን ውስጥ ያለው ሃይል ሂደቱን ላለማስቀልበስ ጠንክሮ እየሰራ ቢሆንም የተወሰኑ የድርጅቱ አመራሮች ጉባኤውን ለማደናቀፍ እየሰሩ ናቸው ተብሏል።
የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ ስራ አስፈጻሚ አካላት በውጥረት ውስጥ ሆነው በባህርዳር ስብሰባ ላይ መሆናቸው ተነግሯል።
በክልሉ ፕሬዝዳንት ገዱ አንዳርጋቸው ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ምሽቱን ስብሰባ የሚያደርጉት 12ቱ የብአዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከመስከረም 17/2011 ጀምሮ የሚካሄደውን የድርጅቱን ጉባኤ በተመለከተ በአጀንዳዎችና በሪፖርቱ ላይ ሲከራከሩ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
በጭቅጭቅና በንትርክ በተካሄደው ስብሰባ ለውጡን የሚያደናቅፉት የብአዴን አመራር አባላት በማህበራዊ ድረ ገጾች ዘመቻ ተከፍቶብናል ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
በተለይም በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ላይ ያነጣጠረ ትችት ሲያቀርቡ እንደነበር ነው የተነገረው።
የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንንና በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ላይ ባነጣጠረው ግምገማ ከዚህ ቀደም በማስጠንቀቂያ ታልፈው አሁንም አልታረመም ሲሉ ትችት ማቅረባቸው ታውቋል።
በለውጥ አራማጅነትና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው አቶ ደመቀ መኮንን፣አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ዶክተር አምባቸው መኮንንና አቶ ብናልፍ አንዷለም ናቸው።
በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴና በስራ አስፈጻሚነት መቀጠል የሚፈልጉት የሕወሃት አፍቃሪ ብአዴኖች በመስከረም 17 ሊካሄድ የታቀደውን ጉባኤ ለማወክ እየጣሩ ነው ተብሏል።
የብአዴን ስራ አስፈጻሚ አባላት ስብሰባ ቀጥሎ በዛሬው ምሽትም በአመራሮች ላይ ግለሒስ ለማድረግና ድርጅቱን ለማጥራት ውይይት እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው።
በብአዴን ስራ አስፈጻሚነት በአሁኑ ጊዜ በአመራር ላይ የሚገኙት አቶ ደመቀ መኮንን፣አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ዶክተር አምባቸው መኮንን፣አቶ ብናልፍ አንዷለም፣አቶ ጌታቸው አምባዬ፣አቶ አለምነው መኮንን፣ወይዘሮ ዝማም አሰፋ፣አቶ ጌታቸው ጀምበር፣አቶ ለገሰ ቱሉ፣አቶ ከበደ ጫኔ፣አቶ ተፈራ ደርበውና አቶ አህመድ አብተው ናቸው።