በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች “ልጆቻቸውን ይዘው በረሃ ለበረሃ መንከራተቱ እንዲያበቃላቸው” ጠየቁ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች “ልጆቻቸውን ይዘው በረሃ ለበረሃ መንከራተቱ እንዲያበቃላቸው” ጠየቁ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ/ም) ከተለያዩ የአማራ ክልል የገጠር አካባቢዎች ተጉዘው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በእርሻ እና በሌሎችም ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአማራ ተወላጆች፣ በክልሉ ውስጥ የሚደርስባቸው በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን ኢሳት ያነጋገራቸው የክልሉ ተወላጆች ገልጸዋል።
“በአንዳንድ ወረዳዎች ብቻ በያመቱ ከ30-50 የሚጠጉ የአማራ ተወላጆች በሰበብ አስባቡ ይገደላሉ” የሚሉት ነዋሪዎች፣ ችግሮቹን ሁሉ እየተቋቋሙ በክልሉ መቆየትን እንደመረጡ የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ “ ካራ እንደተሳለላት በግ ጊዜያችንን እየጠበቅን ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ይናገራሉ።
ህዝቡ እየተጎዳ ቢሆንም፣ ወደ ክልላችን መመለስ እንኳን አንችልንም የሚሉት የአማራ ተወላጆች፣ በክልላችን፣ “ እንኳንስ አርሰን ልንበላ የምንቀመጥበት መሬት እንኳን እያጣን ነው” ይላሉ
“የአማራ ህዝብ መቀመጫ አላገኘም፣ ሁሌም ተሳዳጅ ሆኗል። ልጆቻችንን ይዘን በረሃ ለበረሃ መንከራተት እጣ ፋንታችን ሆኗል” የሚሉት ነዋሪዎች፣ “መንግስትም ህዝቡን ጠልቶታል” ሲሉ ይናገራሉ። “እኛ መውጫ አጥተን አሁንም ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚሄዱት የአማራ ተወላጆች ቁጥር ከፍተኛ” መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ሁሌም የስጋት ህይወት እንድንኖር ተፈርዶብናል በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል።
በቅርቡ በካማሽ ዞን በበለው ጀጋንፎ ወረዳ እንዲሁም በኦሮምያ ክልል በቡኖ በደሌ፣ በጅማና ነቀምቴ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከ500 በላይ ሰዎች በባህርዳር ከተማ ቤተክርስቲያን ተጠልለው ይገኛሉ። የክልሉ መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፣ እስካሁን መፍትሄ ሊያገኙ እንዳልቻሉ የክልሉ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ዘግቧል።
የአማራ ክልል ባለስልጣናት ተፈናቃዮች ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲመለሱ ካልሆነም ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ መጠየቁን ቢገልጽም፣ ተፈናቃዮች ግን እንኳንስ ወደ ተፈናቀሉበት ቦታ ሊመለሱ ቀርቶ ከተጠለሉበት ቦታ እንኳን በወታደሮች ተገደው እንዲወጡ መደረጋቸውንና አማራጭ በመጣታቸው በቤተክርስቲያን መጠለላቸውን ይናገራሉ።