በቤንሻንጉል ካማሽ ዞን በደረሰ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ አለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 21/2010) በቤንሻንጉል ካማሽ ዞን በደረሰ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ ማለቱን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

በአካባቢው በሺዎች የሚቆጠሩ አማሮች መፈናቀላቸውም ታውቋል።

የችግሩ ሰለባዎችም እስካሁን የሚደርስላቸው አካል እንዳላገኙ ተናግረዋል።

የብአዴን ወኪሎች ወደ አካባቢው ቢመጡም ችግሩ ከሚገለጽ ይልቅ ቢሸፋፈን መምረጣቸውን ተፈናቃዮቹ አስታውቀዋል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የብሔር ግጭት ለማስነሳት በግለሰቦች ጸብ ስም በሺዎች የሚቆጠሩ አማሮች እንዲፈናቀሉ ተደርጓል።

በክልሉ ካማሽ ዞን ግጭቱን ተከትሎ በተፈጸመው ጥቃት እስካሁን ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውንም የአካባቢው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ለኢሳት እንደገለጸው በአካባቢው ከተጀመረው ጅምላ ግድያ ለማምለጥ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ በሺዎች የሚቆጠሩ አማሮች አካባቢውን ለቀው ሸሽተዋል።

ከጥቃቱ ለመከላከል የአካባቢው የመንግስት አካላት ሕዝቡን ከመጠበቅ ይልቅ ችግሩ እንዲባባስ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለዋል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቀሉ አማሮችን ለመመልከት ብአዴን ወኪሎቹን ወደአካባቢው ቢልክም ችግሩ እንዲደበቅና እንዳይወጣ የመሸፋፈን ስራ እየሰራ መሆኑን በአካባቢው ችግሩ የደረሰባቸው ሰዎች ገልጸውልናል።

በወረዳው ብአዴንን ወክሎ የሚገኘው ግለሰብም አስከሬን እንዳይነሳና ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ እንዳይታይ መረጃ እንዳይሰበሰብ አስጠንቅቆናል ነው ያሉት።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በርካታ ሰዎች ተገድለው ወደ ገደል ተጥለዋል ያሉት የአይን እማኞች አስከሬኖችን እንዳናነሳም ተከልክለናል ነው ያሉት።

እናም በአካባቢው እየደረሰብን ያለውን ስቃይ መነሻ በማድረግ ሕዝብ ይድረስልን ሲሉ ተመጽነዋል።

በኦሮሚያ ኢሉባቡር ዞንም በተመሳሳይ ሁኔታ በተፈጠረ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ከበስተጀርባ በሕወሃት አባላት የተቀናበረ ነው በተባለው ግጭት ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት ቢሞከርም ሕዝቡ አንድነቱን ጠብቆ ድርጊቱን እየተከላከለ መሆኑን ሲገለጽ ቆይቷል።